ፊዮረንቲና እና ካግሊያሪ ዴቪድ አስቶሪ ይለብሰው የነበረውን 13 ቁጥር ማሊያን ጡረታ አወጡ

የፊዮረንቲናው አምበል ዴቪድ አስቶሪ በድንገት በተኛበት ህይወቱ ማለፉ ተከትሎ የተጫዋቹ ክለብ ፊዮረንቲና እና የቀድሞ ክለቡ ካግሊያሪ አስቶሪ ይለብሰው የነበረውን 13 ቁጥር ማሊያ ከአሁን በኋላ በክለባቸው እንዳይለበስ ጡረታ አወጡ።

እሁድ ፊዮረንቲና ከዩዲኔዜ ጋር ለነበረው ጨዋታ በሆቴል ባረፉበት ውስጥ ሳይታሰብ ህይወቱ አልፎ የተገኘው የዴቪድ አስቶሪ ሞት አነጋጋሪነቱ ቀጥሏል።

ተጫዋቹ ጠዋት ለቁርስ ባለመቅረቡ ስልክ ተደውሎም ባለማንሳቱ ወደ ሆቴሉ የገቡት ጓደኞቹም ህይቱን ማለፉ በማረጋገጣቸው በእለቱ ይደረጉ የነበሩ የሴሪ ኣ ጨዋታዎች በሙሉ መሰረዛቸው ይታወሳል።

በ 10 አመት የሴሪኣው ቆይታ 289 ጨዋታዎችን የተጫወተው አስቶሪ ለጣሊያን ብሔራዊ ቡድንም 14 ጨዋታዎችን መጫወት ችሏል።

በካግሊያሪ ለስድስት አመታትን የተጫወተው አስቶሪ በሮማም በውሰት ቆይታ ያደረገ ሲሆን ከወቅቱ ክለቡ ፊዮረንቲና ጋርም ከ 2015 ጀምሮ ቆይታ አድርጓል።

በዚህ የተነሳ ካግሊያሪ እና ፊዮረንቲና ለተጫዋቹ ክብር ሲባል ከአሁን በኋላ ይለብሰው የነበረውን 13 ቁጥር ማሊያን ጡረታ ማውጣታቸው አሳውቀዋል።

ፊዮረንቲና ከዚህ በተጨማሪ የተጫዋቹን ደሞዝ ለሚስቱ እና ለሴት ልጁ እንደሚከፍል ማሳወቁ ይታወሳል። 

Advertisements