“ከየርገን ክሎፕ ይልቅ ምርጫዬ ለጆሴ ሞውሪንሆ መጫወት ነው”  – ዳኒ ሚልስ 

ዳኒ ሚልስ ከሊቨርፑሉ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ይልቅ ምርጫው በጆሴ ሞውሪንሆ ስር መጫወት መሆኑን ተናግሯል። 

ቀያዮቹ ሊቨርፑሎች ሊጉ ሊጠናቀቅ ዘጠኝ ጨዋታዎች ብቻ በቀሩበት በዚህ ወቅት በመጪው ቅዳሜ ምሳ ሰዓት በሁለት ነጥብ በልጦ ከላያቸው የተቀመጠውን የምንግዜም ተቀናቃኛቸው ማንችስተር ዩናይትድን ለመግጠም ወደኦልትራፎርድ ያመራሉ። 

የቀድሞው የማንችስተር ሲቲ ተጫዋች ሚልስም ሞውሪንሆ ባላቸው የሰው አስተዳደር ብቃት እና የሚከተሉት በመከላከል ላይ ያመዘነ አጨዋወት ስለሚመቸው ምርጫው ከፖርቹጋላዊው የኦልትራፎርድ አለቃ ጋር መስራት መሆኑን ገልጿል።

ሚልስ “ለሞውሪንሆ ብጫወት እወድ ነበር። አውቃለሁ እሱን መምረጤ ብዙ ነገሮችን ያስነሳል። ነገርግን ጆሴ በቀደመው የአሰልጣኝነት ዘመኑ ነገሮችን የሚጋፈጥበት፣ የታክቲካል ብቃቱ እና ለለውጥ ያለው ፍላጎት አስደሳች ነበር።

“ለእኔ በሚመች መልኩም እሱ የመከላከል አጨዋወትን የሚከተል ነው። ነገርግን ጆሴ እራሱን ‘ልዩ ሰው’ በማለት ለብዙ ጊዜያት እራሱን ሰቅሎ ቆይቷል።” በማለት ለዕለታዊው ‘ፕሪምየር ሊግ ዴይሊ’ አስተያየቱን ሰጥቷል።

ሚልስ በንግግሩ ክሎፕ በመከላከል ላይ ትልቅ ትኩረት አለመስጠታቸው ሞውሪንሆን እንዲያስቀድም እንዳደረገው እና ውሳኔው በግል ምርጫው ላይ የተመሰረተ ቢሆን ለዩናይትዱ አለቃ ቅድሚያ እንደሚሰጥ አስረግጦ ተናግሯል።

ዳኒ ሚልስ በዋነኛነት በቀኝ ተከላካይ ሚና በተጨማሪነት ደግሞ በመሀል ተከላካይነት ሚና በቀድሞው ሀያል ክለብ ሊድስ ዩናይትድ ቆይታው ተለይቶ የሚታወስ ሲሆን በጉልበት ጉዳት የተነሳም በ 2009 ገና በ 30ዎቹ መጀመሪያ እድሜው ራሱን ከእግር ኳስ ማግለሉ አይረሳም።

እንግሊዛዊው የቀድሞ ኮከብ ከሊድስ እና ሲቲ በተጨማሪ ለኖርዊች፣ ለቻርልተን አትሌቲክ፣ ለሚድልስብሮ፣ ለሁል ሲቲ እና ደርቢ ካውንቲ የተጫወተ ሲሆን በአጠቃላይ በክለብ ደረጃ 321 ጨዋታዎችን አድርጎ ሰባት ግቦችን አስቆጥሯል።

Advertisements