“400 ሚልዮን ለዝውውር ብናወጣም አልቻልንም ” – ሁሊያን ድራክስለር

​የፈረንሳዩ ቱጃር ክለብ ፓሪስ ሴንት ጀርሜይን ትናንት ምሽት በተደረገው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የጥሎ ማለፍ የመልስ ጨዋታ በስፔኑ ሪያል ማድሪድ መሸነፉን ተከትሎ ጀርመናዊው አማካይ ድራክስለር የክለቡን አሰልጣኝ ሁናይ ኤምሬ በነገር ሸንቆጥ አድርጓል፡፡

ፔዤ በመጀመሪያው ጨዋታ በሳንቲያጎ በርናባው የ 3 ለ 1 ሽንፈትን አስተናግዶ የነበረ ቢሆንም በሜዳው ፓርክ ደ ፕሪንስ በሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ውጤቱን ለመቀልበስ እንደሚታትር የበርካታ የክለቡ ደጋፊዎች ተስፋ ነበር፡፡

ሆኖም በጨዋታው ክለቡ ውጤቱን ለመቀልበስ ሲያሳይ የነበረው ተጋድሎ አናሳ ከመሆኑም በላይ ለሽንፈት መጋለጡ የክለቡን ደጋፊዎች ያስቆጣ ሲሆን ድራክስለርም የደጋፊዎቹን ቁጣ የሚደግፍ አስተያየት ሰጥቷል፡፡

ለስካይ ስፖርት ሃሳቡን ያካፈለው ተጫዋቹ “ከተማው ተማሙቆ ነበር ፤ እኛም ጥሩ የማሸነፍ ስሜት ይዘን ነበር፡፡ሜዳ ላይ የታየው ግን ይህ አይደለም፡፡ ኳስን መቆጣጠር ብቻውን ዋጋ የለውም፡፡ የጎል ብልጫ እንደተወሰደበት ቡድን ተጋጣሚያችን ላይ ጫና ማሳደር ይገባን ነበር ” ብሏል፡፡

አማካዩ ቀጥሎም “በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከ 400 ሚልዮን ፓውንድ በላይ ወጪ አድርገን ኮከቦችን ስናስፈርም ብዙዎች ነገሮችን ልንለውጥ እንደምንችል አስበው ነበር፡፡ ምንም ለውጥ መፍጠር ባለመቻላችን ከውድድሩ ውጪ መሆናችን የሚገባን ነው ” ሲል አክሏል፡፡

በጨዋታው 76ኛ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወደሜዳ የገባው ጀርመናዊ በአሰልጣኝ ኡናይ ኤምሬ ሃሳቦችና ውሳኔዎች ላይ ጥያቄ እንዳለውም አልሸሸገም፡፡

እንደድራክስለር ገለፃ “ወደሜዳ ለመግባት አሟሙቄ ተዘጋጅቼ ነበር ፤ ልክ ካቫኒ የአቻነቷን ጎል ሲያስቆጥር ወደተጠባባቂ ወንበር እንድመለስ ተደረገ፡፡ ለምን እንደሆነ አልገባኝም ጨዋታውን ለማሸነፍ ተጨማሪ ጎሎች እያስፈለጉን አቻ ስለሆንን ብቻ የማጥቃት ሃሳብን መሰረዝ ትርጉሙ ግልፅ አልሆነልኝም፡፡ ተገርሜያለሁ ፡፡

Advertisements