ማንችስተር ሲቲ የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊነቱን መቼ ሊያረጋግጥ ይችላል?

አሁን ጥያቄው ማንችስተር ሲቲ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ያነሳ ይሆን? የሚል ሳይሆን መቼ አሸናፊነቱ ሊያረጋግጥ ይችላል? የሚል ሆኗል

የፔፕ ጋርዲዮላው ቡድን ዘጠኝ ጨዋታዎች በቀሩት የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር በሁለተኛ እና በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው የሚከተሉትን ማንችስተር ዩናይትድና ሊቨርፑልን (እንደቅደም ተከተላቸው 16 እና 18 ነጥቦች) ቀድሞ በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ በቀዳሚነት ተቀምጦ ይገኛል።

የፊታችን ቅዳሜ ዩናይትድና ሊቨርፑል እርስ በእርስ ተገናኝተው የሚጫወቱ በመሆናቸው ደግሞ ቅድመ ግምቱን ውስብስብ ያደረገዋል። ይሁን እንጂ ሲቲ ቅዳሜ መጋቢት 29፣ 2010 ዓ.ም ከቀንደኛ ጠላቱ ዩናይትድ ጋር በኢትሀድ በሚያደርገው ጨዋታ አሸናፊነቱን ይፋ የሚያደረግበትም መልካም አጋጣሚ አለው።

ከዚያ በፊት የሚያሸንፍ ከሆነ ደግሞ በዚያ ጨዋታ ላይ ዩናይትድ እየመረረውም ቢሆን ለተቀናቃኙ በክብር ግራና ቀኝ በመቆም የአድናቆት ጭብጨባ ወደሜዳ እንዲገባ አቀባበል ሊያደርግለት ይገደዳል።

ሁኔታው ውስብስብ በመሆኑ ፅሁፉን በትኩረት እንዲያነቡ እናሳስባለን።

የመሆን ዕድል 1 – ሲቲ መጋቢት 22 ኤቨርተንን የሚያሸንፍ ከሆነ


ሊቨርፑል የፊታችን ቅዳሜ ዩናይትድን የሚያሸንፍ ከሆነ እና መጋቢት 8 በዋትፎርድ የሚሸነፍ ከሆነ፣ ሲቲ ስቶክን የፊታችን ሰኞ በማሸነፍ መጋቢት 22፣ 2010 ዓ.ም በጉዲሰን ፓርክ የዋንጫ ባለቤት መሆኑን ያረጋግጣል።

ይህ እንዲሆን ግን ሲቲ ኤቨርተንን መርታት ብቻ ሳይሆን የዛኑ ቀን (መጋቢት 22) ሊቨርፑል ክሪስታል ፓለስን ዩናይትድ ደግሞ ስዋንሲን እንዳያሸንፍ ተስፋ ማድረግ ይጠበቅበታል።

የመሆን ዕድል 2 – ሲቲ መጋቢት 29 ማን ዩናይትድን የሚየሸነፍ ከሆነ


የመጀመሪያው ዕድል የሚሆን ከሆነ ሲቲ ባለው ሰፊ የግብ የበላይነት የዋንጫው ባለቤት መሆን ይችላል። ነገር ግን ሊቨርፑል ክሪስታል ፓላስን የግድ ማሸነፍ ይኖርበታል።

ይሁን እንጂ ዩናይትድ ሊቨርፑልን ቢያሸንፍ አሊያም በአቻ ውጤት ቢለያይ እና በስዋንሲ ቢሸነፍ ከለይ የተገለፀው ነገር ሊፈጠር ይችላል። ይሁን እንጂ በዚህኛው የመሆን ዕድል የማንችስተር ደርቢ በተከታዩ ሳምንት እስኪካሄድ ድርስ ሂሳባዊ ማረጋገግጫ ላይቀርብበት ይችላል።

ሌላኛው ይበልጥ የመሆን ዕድል የሚፈጠረው ደግሞ ዩናይትድ በመጪው ቅዳሜ ሊቨርፑልን ቢያሸንፍ ወይም አቻ ቢለያይ ከዚያም ስዋንሲን መጋቢት 22 ቢያሸንፍ እና መጋቢት 29 በሲቲ የሚሸነፍ ከሆነ ነው።

የመሆን ዕድል 3 – መጋቢት 30 ከመርሲ ሳይድ ደርቢ ውጤት በኋላ


የሲቲ ደጋፊዎች ክለባቸው በጨዋታ ላይ እያለ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ መሆናቸውን ቢያረጋግጡ ፍላጎታቸው እንደሆነ እርግጥ ነው። ነገር ግን መጋቢት 30 የሚደረገውን የመርሲሳይድ ጨዋታ የመጨረሻ ውጤት ካረጋገጡ በኋላ ዋንጫውን ማሸነፋቸውን የሚያረጋግጡበት ዕድልም አላቸው።

ሊቨርፑል የፊታችን ቅዳሜ ዩናይትድን ከዚያ በኋላ ደግሞ ዋትፎርድና ፓላስን የሚያሸንፍ ከሆነ (በተመሳሳይ ሲቲ ስቶክን፣ ኤቨርተንን እና ዩናይትድን የሚያሸንፍ ከሆነ) በ18 ነጥቦች የሚርቅ ይሆናል።

የማንችስተር ደርቢ ከሚደረግበት ቀን ማግስት ሊቨርፑል ወደኤቨርተን አምርቶ ይጫወታል። ይህ ደግሞ ሲቲን እጁን ወደዋንጫው እንዲዘረጋ ሊያደርገው የሚችል ይሆናል።

ሲቲ ዋንጫውን በዌምብሌይ ሊያነሳ ይችልስ ይሆን?


ሲቲ በቀሪ የጨዋታ ጉዞው በማንኛውም ሁኔታ ነጥቦችን የሚጥል ከሆነ የዋንጫ ድሉ ጉዞውን ሚያዝያ 6 በዌምብሌይ ከቶተንሃም ጋር ወደሚያደረገው ጨዋታ በመግፋት ሊያረጋግጥ ይችላል።

ነገር ግን ሲቲ ከብራይተን ጋር ወይም ዩናይትድ ከዌስት ሃም ጋር የሚያደረጓቸው የጨዋታ መርሃግብሮች የተረጋገጠ ቀን ስላልተቆረጠላቸው በጨዋታው ቀን ላይ ለውጥ ሊኖር ስለሚችል የሲቲ የዋንጫ ድል ቀንም ለውጥ ሊገጥመው ይችላል።

በእርግጥ ሲቲዎች በቀጣዮቹ ሳምንታት በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች በሚገጥማቸው ሽንፈት ነጥባቸውን ከተከታዮቻቸው ዩናይትድና ሊቨርፑል የሚያጠቡ ከሆነ የዋንጫ ድል የደስታ ፌሽታቸውን ከታሰበውም ጊዜ በላይ ለተጨማሪ ጊዜያት ወደፊት ሊገፉት ይችላሉ። ሲቲዎች ከሚያዝያ 6 በኋላ የሚቀሯቸው ጨዋታዎች ደግሞ ከስዋንሲ (በሜዳቸው – ሚየዝያ 14)፣ ከዌስትሃም (ከሜዳቸው ውጪ -ሚያዝያ 22)፣ ከኸደርስፊልድ (በሜዳቸው – ሚያዝያ 27)፣ ከሳውዛምፕተን (ከሜዳቸው ውጪ-ግንቦት 5) እና ከብራይተን (በሜዳቸው -ቀኑ አልታወቀም) የሚያደርጓቸው ናቸው።

አዲስ ክብረወሰን


ብዙ ጨዋታ እየቀረ በጊዜ ዋንጫ ከማንሳት አኳያ ሲቲ ሰባት ጨዋታዎች እየቀረው በኤቨርተን ሜዳ በማሸነፍ ወይም ስድስት ጨዋታዎች እየቀረው በሜዳው ዩናይትድን በማሸነፍ አዲስ የፕሪሚየር ሊግ ክብረወሰን ማስመዝገብ ይችላል።

ዩናይትድ ይህን ክብረወሰን በሚቀሩ አምስት ጨዋታዎች በ1999/00፣ በ2000/1 ከዚያም በ2012/13 ሁለት ጊዜ መያዝ ሲችል፣ በ2003/04 የውድድር ዘመን ለሽንፈት ያልተበገረው የአርሰናል ቡድንም ይህንኑ ክበረወሰን ተጋርቷል።