ቅ/ጊዮርጊስ ከ ኬሲሲኤ ጋር አቻ ሲለያይ ወላይታ ድቻ ዛማሌክን አሸነፈ

በአዲስ አበባ እና በሀዋሳ ስታድየም የተደረጉ የአፍሪካ ቻምፕየንስ ሊግ እና የኮንፌዴሬሽን ጨዋታዎች ፈረሰኞቹ ያለ ግብ አቻ ሲለያዩ ወላይታ ድቻ በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ሰፊ ልምድ ያለውን ዛማሌክን አሸነፈ።

ኢትዮጵያን በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ላይ ወክለው እየተሳተፉ የሚገኙት ቅ/ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ ወደ ምድብ ድልድሉ ውስጥ ለመግባት እየተደረጉ የሚገኙ የማጣሪያ ጨዋታዎች የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በሜዳቸው አከናውነዋል።

በአ/አ ስታድየም ፈረሰኞቹን ለመደገፍ በስታድየሙ የተገኙት የክለቡ ደጋፊዎች ተጨዋቾቹ ወደ ሜዳ ሲገቡ ያሳዩት ደማቅ ያማረ የድጋፍ ትእይንት ክለባቸውን በማነቃቃት ጨዋታው ተጀምሯል።

በጨዋታው መጀመሪያ ላይ የነበረው የደጋፊዎች ድባብ

ፈረሰኞቹ አዲስ ፈራሚው እና የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው ማሊያዊው አማራ ማሌን በመሀል አጥቂነት በማጫወት 433 አጠቃቀምን ይዞ ለጀመረው የቫስ ፒንቶ ቡድን አቢበከር እና ጋዲሳን በመስመር አጥቂነት በማድረግ ተጫውቷል።

በፈጣን እንቅስቃሴ በማድረግ የጀመረው አማራ ማሌም የሚላኩለትን ረጅም ኳሶች ከሌሎች በተሻለ የኬሲሲኤ ተከላካዮችን ለማስጨነቅ ቢሞክርም እንቅስቃሴው ከመጀመሪያው 15 ደቂቃዎች ያለፈ ሊሆን አልቻለም።

አስቻለው ታመነ ባለሜዳዎቹ በጊዜ መምራት የሚችሉበትብ ጥሩ አጋጣሚ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣበት ኳስ እንዲሁም ሳልሀዲን በርጊቾ የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውስጥ ሚዛኑን ሳይጠብቅ ወደ ጎል ለመምታት ሞክሮ ያልተሳካበት አጋጣሚ ይጠቀሳሉ።

በዚህ የመጀመሪያ ግማሽ እንቅስቃሴ እንግዳዎቹ እንደ ሌሎች ቡድኖች በሜዳቸው ተጠቅጥቀው ከመጫወት ይልቅ በፈጣን አጥቂዎቻቸው የፈረሰኞቹ ተከላካዮች ድክመት ታክሎ ያገኟቸውን የማግባት እድሎችን መጠቀም አልቻሉም።

በተለይ የተከላካይ አማካዩ ሙሉአለም መስፍን ፈረሰኞችን ዋጋ ለማስከፈል ተቃርቦ የነበረውን አጋጣሚ ከራሱ የጎል ክልል አካባቢ ተቀምቶ  ፖል ሙኩሪዚ ሞክሮ ኦዶንግካራ የመለሰው ወርቃማ አጋጣሚ ይጠቀሳል።

ኬሲሲኤ በንስምባምቢ አማካኝነትም ሌላ ቆንጆ ጎል የማግባት አጋጣሚን ቢያገኙም በተመሳሳይ በግብ ጠባቂው ሮበርት ኦዶንግካራ የነቃ እንቅስቃሴ ተመልሷል።

በሁለተኛው ግማሽ ሙሉአለም መስፍንን ቀይረው ታደለ መንገሻን በማስገባት ጎል ለማግባት ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳይ ቅያሬ ያደረጉት ፈረሰኞቹ ለረጅም ወራት ጉዳት ላይ ከነበረው ታደለ መንገሻ እንቅስቃሴ ተጠቅመዋል ለማለት ያስቸግራል።

ተጫዋቹ ከጉዳት እንደመመለሱ እና በጨዋታዎች እራሱን ወደ ቡድኑ እንቅስቃሴ የሚያዋህድበት አጋጣሚዎ ሳይፈጠሩ በጠንካራው መድረክ እንዲጫወት መደረጉ ለቡድኑ ጥቅም ሲሰጥ አልታየም።

በተመሳሳይ ባለሜዳዎቹ የመጨረሻዎቹን 20 ደቂቃዎችም ሌላው ጉዳት ላይ የነበረው ሳልሀዲን ሰኢድን በመቀየር አማራ ማሊን ወደ ግራ መስመር በማውጣት ጎል ለማስቆጠር ቢያስቡም የነበራቸው ደካማ እንቅስቃሴ ጨዋታው ከአቻ በላይ እንዳይዘል አድርጎታል።

በሁለተኛው ግማሽ ሳይጠቀስ መታለፍ የሌለበት አጋጣሚ የነበረው ሳልሀዲን ሰኢድ ከግራ መስመር የተሻገረለትን ብቻውን በጭንቅላት ሸርፎ ለማግባት ሞክሮ ለመጠቀም ያልቻለበት አጋጣሚ ነበር።

ባለሜዳዎቹ በሙሉ የጨዋታ እንቅስቃሴ ካገኟቸው ውስን ጎል የማግባት አጋጣሚዎች ውስጥ እጅግ የተሻለው ይህችው ሳልሀዲን በጭንቅላት ያልተጠመባት ኳስ ነበረች።

ዴሪክ ኒሲምባምቢ ከቀኝ መስመር የተሻገለትን ኳስ በጭንቅላቱ ሞክሮ የላይኛው አግዳሚ ገጭቶ የወጣው አጋጣሚ ለኬሲሲኤ በሁለተኛው አጋማሽ ከመኮሯቸው አጋጣሚዎች የተሻለው ነበር።

የዩጋንዳው ሻምፕዮን ወደ አ/አ መጥቶ ማሸነፍ እንደሚከብደው ቢረዳም በጨዋታው የነበራቸው እቅድ ሽንፈትን ለማስወገድ ወይንም በጠባብ ውጤት ለመሸነፍ ነበር።

ነገርግን በጨዋታው የነበራቸው የተሻለ ጎል የማግባት አጋጣሚዎች ሲታወሱ ጨዋታውን እዚሁ ጨርሰውት የሚሄዱበት እድል እንደነበራቸው በማስተዋል የመልሱ የሜዳቸው ጨዋታ ለፈረሰኞቹ ከባድ ፈተና ሊሆኑ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል።

ፈረሰኞቹ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ፕሪምየርሊግ እያሳዩት የሚገኙትን ደካማ እንቅስቃሴ በአፍሪካ መድረክ ተከትሏቸው መጥቷል።

የነበራቸው አጠቃላይ እንቅስቃሴ የተበታተነ እና ቅርፅ ያልነበረው ነበር።ረጃጅም ኳሶቻቸውም ቢሆኑ በተቃራኒ ቡድን ተከላካዮች በቀላሉ ሲመለሱ ታይተዋል።

ጨዋታው ያለ ጎል በመጠናቀቁ የመልሱ ጨዋታ በጉጉት እንዲጠበቅ የሚያደርገው ሲሆን ፈረሰኞቹም በመልሱ ጨዋታ በተለይ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን እና በተከላካይ መስመር ላይ የሚሰሯቸው ስህተቶች የሚያሻሽሉ ከሆኑ አሁንም ወደ ምድብ ድልድሉ የመቀላቀል እድሉ በራሳቸው እጅ ላይ እንደሚገኝ መናገር ይቻላል።

በሌላው የአፍሪካ የኮንፌዴሬሽን ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ እየተሳተፈ የሚገኘው ወላይታ ድቻ በአፍሪካ የገነነ ስም ያለውን ዛማሌክን በሀዋሳ አለም አቀፍ ስታድየም 2-1 አሸንፏል።

ዛማሌክ ምንም እንኳን በግብፅ ፕሪምየርሊግ የአል አህሊን ጠንካራ አቋም መቋቋም ባይችልም ኢሀብ ጋላልን ከቀጠሩ በኋላ ያለፉት ስድስት ተከታታይ የሊጉን ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችለዋል።

ነገርግን ምንም እንኳን ደረጃቸውን ከአል አህሊ በመቀጠል በሁለተኛ ደረጃ ላይ ቢገኙም በነጥብ በጣም በመራቃቸው ትኩረታቸውን የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ማሸነፍን አድርገዋል።

አሰልጣኙ ከሰሞኑን በሰጡት አስተያየት ቡድናቸው ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾች አንዳንዶቹ በአፍሪካ መድረክ ላይ ልምድ የሌላቸው ቢሆንም ጠንካራ አጀማመር እንደሚያደርጉ ተናግረው ነበር።

በሀዋሳ ስታድየም ከጎረቤት ከተሞች ጭምር በመምጣት የደቡቡን ቡድን ሲያበረታቱ የነበሩ ደጋፊዎች ያስደሰተ ውጤት ላስመዘገበው ድቻ ሁለቱን ጎሎች በዛብህ እና ያሬድ አስቆጥረዋል።

ዛማሌኮች ሽንፈት በማስተናገዳቸው በሜዳቸው የሚያደርጉትን የመልስ ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል።

የመልስ ጨዋታውም በስዊዝ የጦሩ ሜዳ ላይ እንዲካሄድ ቀደም ብለው የጠየቁት ዛማሌኮች እስከ 20ሺ የሚቆጠር ደጋፊዎቻቸው ወደ ስታድየም እብዲገቡም ጥያቄ ቢያቀርቡም ፍቃድ ያገኙት ግን ለ 5ሺህ ደጋፊዎቻቸው ብቻ እንደሆነ ተሰምቷል።

ይህ በስታድየም የሚገኘው የዛማሌክ አነስተኛ የሆነ የደጋፊ ቁጥርም በመልሱ ጨዋታ ላይ ወላይታ ድቻ ከሜዳው ውጪ የመጫወት ስሜት እንዳይሰማው የሚያደርገው በመሆኑ ታላቁን ቡድን ወደ ኋላ ተመልክቶ ወደ ምድብ ድልድሉ ሊገባ የማይችልበት  ምንም አይነት ምክንያት ስለማይኖር የመልሱ ጨዋታ ከወዲሁ ተጠባቂ አድርጎታል።

Advertisements