“በቻምፕየንስ ሊጉ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ሊቨርፑል የእንግሊዝ ቡድኖችን ማሸነፍ ይችላል”-ፊርሚኖ

የሊቨርፑሉ የአጥቂ መስመር ተሰላፊው ሮቤርቶ ፊርሚኖ ሊቨርፑል በቻምፕየንስ ሊጉ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ የእንግሊዝ ቡድኖች ቢገጥሙት አሸንፎ ወደ ግማሽ ፍፃሜው መቀላቀል እንደሚችል ተናግሯል።

ሊቨርፑልማክሰኞ በተደረገው የቻምፕየንስ ሊጉ ጨዋታ ከፖርቶ ጋር በሜዳው ያለጎል ቢለያይም ከሜዳው ውጪ 5-0 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፉ ዘና ብሎ ወደ ሩብ ፍፃሜው ተቀላቅሏል።

ሌላው የእንግሊዝ ክለብ የሆነው ማን ሲቲም እንዲሁ ብዙም ሳይቸገር ወደ ሩብ ፍፃሜ የተቀላቀለ ሌላኛው የእንግሊዝ ቡድን ቢሆንም ቶተንሀም በሜዳው በመሸነፉ ወደ ሩብ ፍፃሜ ሳይቀላቀል ቀርቷል።

ቼልሲ እና ማን ዩናይትድ ደግሞ በቀጣይ ሳምንት የሚያደርጉት ጨዋታ የማለፍ እድላቸውን የሚወስኑ ቢሆንም በተለይ ቼልሲ ባርሴሎናን አሸንፎ የማለፍ እድሉ ጠባብ ይመስላል።

እንግሊዞች በሩብ ፍፃሜው በስንት ቡድኖች እንደምወከሉ ባይታወቅም የሊቨርፑሉ አጥቂ ሮቤርቶ ፊርሚኖ ማንኛውም የእንግሊዝ ቡድን ማሸነፍ እንደሚችሉ ተናግሯል።

“አዎ ከእንግሊዝ ክለቦች ጋር እንዲደርሰን እንፈልጋለን።ለምን አንፈልግም?ባለፉት ጥቂት አመታት የእንግሊዝ ቡድኖችን ማሸነፍ እንደምንችል አሳይተናል።

“ከነሱ ጋር ያለን ሪከርድ ጥሩ ነው።ከእንግሊዝ ክለቦች ጋር ስንጋጠም ጥሩ ጨዋታ መጫወት እንደምንችል በራሳችን እምነት አለን ማሸነፍ እንደምንችልም አሳይተናል።

ፊርሚኖ ጨምሮ የስፔን ክለቦች ቢደርሳቸው እንኳን እንደማይፈሩ ነው የተናገረው።

“ማንም ቢደርሰን አንጨነቅም።የስፔን ትላልቅ ቡድኖች?እኛ አንፈራም።ማንንም የምንፈራበት ጊዜ አይደለም።በዚህ ደረጃ ከደረስክ ማንንም መፍራት የለብንም፣ማንንም ቡድን ማሸነፍ እንደምንችል ይሰማናል፣እኛ ሌላ ቡድንን ችግር ውስጥ መክተት እንደምንችል አስባለው።በርግጥ ሁሉም ቡድን ጠንካራ ነው ነገርግን ይህ እኛን አያስጨንቀንም።” ሲል ተናግሯል።

የአውሮፓ ቻምፕየንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ድልድል በቀጣይ አርብ የሚታወቅ ይሆናል።

Advertisements