ወጣቱ የቀድሞ የአርሰናል ተጫዋች ከ29 አመታት በኋላ የባርሴሎናን መለያ ለብሶ መጫወት የቻለ እንግሊዛዊ ሆነ

​የ19 አመቱ የቀድሞ የአርሰናል ታዳጊ ማርከስ ማክጉዋን ከጋሪ ሊንከር በኋላ የካታላኑን ባርሴሎና መለያ ለብሶ መጫወት የቻለ እንግሊዛዊ በመሆን ታሪክ ሰርቷል፡፡

ትናንት ምሽት በስፔን የጥሎ ማለፍ ዋንጫ የመልስ ጨዋታ በባርሴሎናና በኢስፓኞል መካከል ተካሄዶ ባርሴሎና ጨዋታውን በመለያ ፍፁም ቅጣት ምት በመርታት ወደቀጣዩ ዙር ያለፈ ሲሆን በ76ኛው ደቂቃም ታዳጊው እንግሊዛዊ ለዋናው የባርሰሎና ስብስብ ለመጀመሪያ ጊዜ መጫወት ችሏል፡፡

በጥሩ የዝውውር መስኮት አርሰናልን ለቆ የባርሴሎናን ሁለተኛ ቡድን የተቀላቀለውና ውል ማፍረሻ  25 ሚልዮን ዩሮ የተለጠፈበትን ስምምነት የተፈራረመው ማክጉዋን ጨዋታው የተለየ ስሜት ፈጥሮበት እንዳለፈ አልሸሸገም፡፡

ተጫዋቹ እንደተናገረው ” በጥር ወደዚህ ስመጣ ከጋሪ ሊንከር በኋላ ለብሉግራናዎቹ የተጫወተ እንግሊዛዊ ልሆን እንደሆነ ብዙ ሰው ይነገርኝ ነበር ፤ ስለሆነም ያንን ቀን በባርሳ ሁለተኛ ቡድን ሆኜም እጠብቀው ነበር፡፡ አሰልጣኙ ልገባ እንደሆነና እንድዘጋጅ ሲነግረኝ ተረጋግቼ ምን ማድረግ እንደምችል ለአለም ማሳየት ፈለግኩ፡፡” በማለት ስሜቱን አብራርቷል፡፡

ዝነኛው የቀድሞ ኮከብ ጋሪ ሊንከር በ1986 ኤቨርተንን በመልቀቅ ወደባርሴሎና ካመራ በኋላ በዋንጫ ድሎች የታሰበ ቆይታ የነበረው ሲሆን በ1989 ክለቡን ሲለቅ ከ50 በላይ ጎሎችን አስቆጥሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡

Advertisements