እርምጃ / ፔፕ ጋርዲዮላ ከሚያደርጉት ቢጫ ሪባን ጋር በተያያዘ ቅጣት ተላለፈባቸው


አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ቢጫ ሪባን አድርገው ከታዩበት ክስተት ጋር በተያያዘ 20,000 ፓውንድ የተቀጡ ሲሆን በቀጣይም ተግባሩን እንዳይደግሙት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

የማንችስተር ሲቲው አለቃ ሪባኑን በጋዜጣዊ መግለጫና በሜዳ ላይ አድርገው የታዩት በካታላን ግዛት ለታሰሩ አራት ፓለቲከኞች ድጋፍ ለማሳየት ነው። 

በካታሎኒያ የተወለዱት ስፔናዊው አሰልጣኝ ድርጊትም በብዙዎች ዘንድ ክርክርን ያስነሳ ሲሆን እራሳቸው ፔፔም  ድርጊቱ ፖለቲካ ይዘት የለውም በማለት ሲከራከሩ ታይተዋል። 

ነገርግን የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር ደንብ የፓለቲካ ይዘት የሚያንፀባርቁ ሪባኖች ማድረግ ስለሚከለክል ህጉን በማክበር በቀጣይ አድርገውት ወደሜዳ እንደማይገቡ ጋርዲዮላ አስታውቀዋል። 

በሌላ በኩል ግን የእግር ኳስ ማህበሩ ደንብ ሪባን ማድረግን የሚከለክለው በሜዳ ውስጥ ባለው የቴክኒካል ስፍራ ብቻ በመሆኑ ጋርዲዮላ ከቅድመ እና ድህረ ጨዋታ በኃላ በሚደረጉ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ አድርገውት እንደሚገቡ ተነግሯል።

ከዚህ በተጨማሪም የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በሪባን ዙሪያ ክልከላ ስለሌለው ባሳለፍነው ረቡዕ ከባሴል ጋር እንዳደረጉት የኢትሀዱ አለቃ ሪባኑን በቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ላይ ማድረጋቸውን የሚቀጥሉ ይሆናል። 

ጋርዲዮላ ሪባን ማድረግ የጀመሩት ባሳለፍነው ጥቅምት ወር በካታሎኒያ የተደረገውን የራስ ገዝ ህዝበ ውሳኔ በስፔን ማዕከላዊ መንግስት ህገወጥ መባሉን ተከትሎ ነው። 

የኢትሀዱ አለቃ ከሪባኑ ጋር በተታያዘ ክስ የቀረበባቸው ባሳለፍነው ወር ከዊጋን ጋር በነበረው የኤፍኤ ዋንጫ ጨዋታ በኋላ ሲሆን ከዛ ወዲህ ሪባኑን ወይ አርገውት አይገቡም አሊያም ወደሜዳ ሲገቡ ሸፍነውት ይገባሉ። 

Advertisements