“የአርሰናል ቆይታዬ አልተረጋገጠም ” – ጃክ ዊልሸር

ከአንድ አመት የውሰት ቆይታ በኋላ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ወደእናት ክለቡ አርሰናል የተመለሰውና ቀስ በቀስም በቡድኑ ውስጥ የቋሚ ተሰላፊነት ቦታውን የተረከበው እንግሊዛዊ አማካይ ጃክ ዊልሸር በመድፈኞቹ ቤት ያለው ቆይታ እስካሁን እንዳለየለት አሳውቋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያሳየ የመጣውን መልካም አቋም ተከትሎ ከአርሰናል የውል ማራዘሚያ እንደቀረበለት አርሰን ዌንገር አሳውቀው የነበረ ሲሆን አንዳንድ ሪፖርቶች ግን ዊልሸር ከነበረው የደመወዝ መጠኑ ቀንሶና ጨዋታዎችን ባደረገ ቁጥር በጉርሻ መልክ ተጨማሪ ገንዘብ እንዲከፈለው የሚጠይቅ ውል እንደቀረበለትና ያንን ውል ለመቀበል ግን እንዳንገራገረ ጠቁመዋል፡፡
የ26 አመቱ አማካይ ተደጋጋሚ ጉዳቶች የሚጠበቅበትን ያህል ስኬት እንዳያገኝ እንዳስገደዱት ብዙዎች የሚስማሙበት ሲሆን ክለቡም ተጫዋቹ ለክለቡ የሚያደርገው የጨዋታ መጠን አሳሳቢ እንደሆነበት ተገልጿል፡፡
አርሰናል ትናንት ምሽት በሳንሲሮ ከተደረገውና ኤሲ ሚላንን 2 ለ 0 ካሸነፈበት የዩሮፓ ሊግ ጨዋታ በኋላ ስለውል ማራዘሚያው ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው አስተያየት “እስካሁን ምንም ያለቀ ነገር የለም ፤ አሰልጣኙ ጥያቄ እንደቀረበልኝ ከተናገሩ ጀምሮ ድርድሮችን ስናደርግ ቆይተናል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ምንም ከስምምነት ላይ የተደረሰበት ነገር የለም ” በማለት ነገሮች ገና መስመር እንዳልያዙ አስታውቋል፡፡

Advertisements