ከዋሊያዎቹ ጋር የተደለደሉት ኬንያዎቹ ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች እንደሚያደርጉ አሳወቁ

​ለ 2019 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከዋሊያዎቹ ጋር በምድብ ስድስት ላይ የተደለደሉት “ሀራምቤ ስታርስ” የሚባሉት የኬኒያ ብሔራዊ ቡድን ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል።ዋሊያዎቹስ?

ለ 2019 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጋና፣ሴራሊዮን፣ኢትዮጵያ እና ኬኒያ በምድብ ስድስት ተደልድለው የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ባለፈው መስከረም ወር ላይ አድርገዋል።

ዋልያዎቹ በጋና መሸነፋቸው የሚታወስ ሲሆን ሴራሊዮን በተመሳሳይ ኬኒያን 2-1 በማሸነፍ ጋና እና ሴራሊዮን ከምድቡ አናት ላይ ተከታትለው ተቀምጠዋል።

የሁለተኛ ጨዋታቸውን ደግሞ በፈረንጆቹ መጋቢት 27 ዋሊያዎቹ ከሴራሊዮን ኬኒያ ደግሞ ከጋና ጋር ያደርጋሉ።

ኬኒያዎቹ ለዚህ ጨዋታ ሲሉ ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ ሲያሳውቁ ተጋጣሚዎቻቸው ደግሞ ኮሞሮስ እና የመካከለኛው አፍሪካ ናቸው።

ሀራምቤ ስታርሶች ለልምምድ በሞሮኮ ከመጋቢት 19 ጀምሮ የሚከትሙ ሲሆን በሞሮኮም ሁለቱን ጨዋታዎች ለማድረግ ቀጠሮ ይዘዋል።

ለዚህ ዝግጅት ደግሞ ተጫዋቾችን የመረጡት ጊዚያዊ አሰልጣኙ ስታንሊ አኩምቢ የቀድሞ የኢንተርሚላን ተጫዋች የነበረውን ማክዶናልድ ማሪጋን ወደ ብሔራዊ ቡድኑ እንዲካተት ጥሪ አድርገውለታል።

የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ የነበሩት ፖል ፑት በቅርቡ ከሀላፊነታቸው ከለቀቁ በኋላ በጊዚያዊ አሰልጣኝነት የሚመሩት ኬኒያዎቹ ከዋሊያዎቹ ጋር መስከረም ወር ላይ የምድባቸው ሶስተኛ ጨዋታን ያደርጋሉ።

በምድቡ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ቡድኖች ይህን ያህል ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም ዋሊያዎቹ ግን ድምፃቸውን ማጥፋታቸው አስገራሚ ሆኗል።

Advertisements