ሞሪንሆ ረሽፎርድን ቀይረው ያስወጡበትን ምክኒያት ገለፁ

ሆዜ ሞሪንሆ ማንችስተር ዩናይትድ ሊቨርፑልን 2ለ1 በረታበት ጨዋታ የዩናይትድን ግቦች ያስቆጠረውን ማርከስ ራሽፎርድን ቀይረው ያስወጡት ጋሪ ኔቭል በጨዋታው አጋማሽ ላይ አጥቂው ቀይ ካርድ ሊመለከት ይገባ እንደነበር የሰጠው አስተያየት በጫዋታው ዳኛ ግሬግ ፓውሰን ላይ ተፅእኖ እንዳያሳድር በመስጋት እንደሆነ ገልፀዋል።

የዩናይትዱ አሰልጣኝ የ20 ዓመቱ ተጫዋች በጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ግቦችን ቢያስቆጥርም በማሩዋን ፌላኒ ቀይረውት በማስወጣታቸው ከደጋፊው ዘንድ ስለደረሰባቸው የተቃውሞ ድምፅ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። ሞሪንሆ በንግግራቸው የቀድሞው የዩናይትድ ተጫዋች ጋሪ ኔቭል በጨዋታ የእረፍት ሰዓት በስካይ ስፖርት የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ አጥቂው በጀምስ ሚልነር ላይ የፈፀመው ጥፋት ቢጫ ካርድ ሳይሆን ለቀይ ካርድ የሚዳርገው እንደነበር ስለሰጠው አስተያየት እንደተነገራቸው ገልፀዋል።

“በእኔ እና በውሳኔዬ ላይ [የተቃውሞ] ምላሽ መቅረቡ ለእኔ ችግር አይደለም። በጨዋታው አጋማሽ አንድ ሰው ጋሪ ኔቭል ማርከስ ራሽፎርድ ቀይ ይገባው እንደነበር ስለመናገሩ ነግሮኛል። እናም ምናልባት ዳኛው በጨዋታው አጋማሽ ላይ ይህን ተመልክቶ በጋሪ ንግግር ተፅእኖ ሊያድርበት ይችላል ብዬ ስጋት ገባኝ። ስለዚህ በሁለተኛው አጋማሽ ሊቨርፑሎች ተጭነውን እኛ ይበልጥ መከላከል ስንጀምር [ለውጡን አደረግኩ]።

“ሊቨርፑሎች በሜዳው መሃል ክፍል ላይ በርካታ ተጫዋቾችን እንዲጫወቱ በማድረግና አሽሊ ያንግን ወደመሃል እንዲሳብ ሲያደረጉት፣ ማርከስ ራሽፎርድ የማዕዘን ስፍራውን ከአሌክሳንደር-አርኖልድ ጥቃት መከላከል ላይ ይገኝ ነበር። በቢጫ ካርዱ እና ጋሪ ቀይ ካርድ ማግኘት እንደሚገባው መናገሩ [በቀይ ካርድ የመሰናበት አደጋ ውስጥ ሳይገባ] በአሌክሳንደር ላይ ጥፋት በመፈፀም የሚጫወት ተጫዋች ለማስገባት ውሳኔ ላይ ደረስኩ።” በማለት ፓርቱጋላዊው አሰልጣኝ ተናግረዋል።

ዳኞች በጨዋታ የእረፍት ሰዓት የጨዋታ ዘገባዎችን እንዲመለከቱ አይፈቀድም። በመሆኑም የሞሪንሆ ይህ ንግግር ጨርሶ ከልባቸው የተናገሩትም አይመስልም።

Advertisements