የተረጋገጠ/ባርሴሎና ብራዚላዊውን ወጣት ኮከብ የግሉ አደረገ

ላ ሊጋውን በሰፊ የነጥብ ልዩነት እየመራ የሚገኘው የካታላኑ ታላቅ ክለብ ባርሴሎና በእንግሊዞቹ ማንችስተር ዩናይትድ ፣ ቼልሲ ፣ አርሰናልና ሊቨርፑል በጥብቅ ሲፈለግ የነበረውን ብራዚላዊ አማካይ በመጪው ሐምሌ ወር ለማስፈረም ከስምምነት መድረሱን አስታወቀ፡፡

ክለቡ በይፋዊ ድረ ገፁ ይፋ እንዳደረገው የ21 አመቱን ወጣት የአማካይ ስፍራ ተጫዋች አርተር ሜሎን ለማስፈረም ያደረገው ጥረት የተሳካ ሲሆን ለፊርማውም 27 ሚልዮን ፓውንድ ለክለቡ ግሪሚዮ የሚከፈል ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ተጫዋቹ በክለቡ ቆይታው የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ብዛት እና ውጤታማነት ታይቶ ተጨማሪ ስምንት ሚልዮን ፓውንድ ለክለቡ እንደሚከፈል ሚረር ይዞት የወጣው ዘገባ አትቷል፡፡

ብራዚላዊው ኮከብ በ2016 ወደግሪሚዮ ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ ለክለቡ 51 ያህል ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን ባለፈው የውድድር አመት የኮፓ ሱዳሜሪካን ፣ የኮፓ ሊቤራዶሪስና የኮፓ ዶ ብረዚል ሻምፒዮን ለነበረው ቡድኑ ወሳኝ ሚናን ሲጫወት ቆይቷል፡፡

ተጫዋቹ ካለፈው አመት ጀምሮ ለወርቃማ ለባሾቹ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን እየተጠራ ሲሆን ሰኔ ላይ ለሚጀመረው የዓለም ዋንጫ አገሩን ከሚወክለው ስብስብ ኣካል በመሆን ወደሩሲያ እንደሚያቀና ይጠበቃል፡፡

Advertisements