የዌስትሃም ዩናይትድ ባለቤቶች የመጫወጫ ሜዳውን ጥሰው በገቡ ደጋፊዎች ስቴዲየም ለቀው ለመውጣት ተገደዱ

ዛሬ ከተደረጉ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል አንዱ በሆነው የዌስትሃምና የበርንሌይ ጨዋታ በክለቡ የውጤት እጦት የተከፉት ደጋፊዎች ወደሜዳ ዘልቀው ከገቡ በኋላ በክለቡ አመራሮች ላይ ተደጋጋሚ ተቋውሞ ማሰማታቸውን ተከትሎ አስተዳዳሪዎቹ ጨዋታው ሳይገባደድ ሜዳውን ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡

የዴቪድ ሞይሱ ስብስብ በሜዳው ለንደን ኦሎምፒክ ስቴዲየም በበርንሌይ 3 ለ 0 የተረመረመ ሲሆን ከመጀመሪያው ጎል መቆጠር ጀምሮ ደጋፊዎች አጥሩን ዘለው በመግባት ጨዋታውን ሲያስተጓጉሉ አምሽተዋል፡፡
በ66ኛው ደቂቃ በርንሌዮች የመጀመሪያ ጎላቸውን ሲያስቆጥሩ አራት ተመልካቾች ወደሜዳ ዘልቀው የገቡ ሲሆን አንደኛው ተመልካች ከክለቡ አምበል ጋር ግብግብ ይዞ ታይቷል፡፡

የበርንሌይ ሁለተኛ ጎል መቆጠሩን ተከትሎ ተመልካቾች የክለቡ ባለቤት የሆኑትት ዳቪድ ሱሌይቫን እና ዳቪድ ጎልድ ወደተቀመጡበት ስፍራ በማምራት “ክለቡን ልቀቁልን” የሚል ተቃውሞን ሲያሳዩ ታይተዋል፡፡

ክለቡ ዌስትሃም ይህንን ድርጊት አስመልክቶ ፈጣን መግለጫ ያወጣ ሲሆን በመግለጫውም ” የክለቡ ውጤት ማጣት ደጋፊዎችን ማሳዘኑ ተገቢ ነው ፤ ግን የተሄደበት መንገድ ህገ ወጥ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ጠንከር ያለ ምርመራና እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን” በማለት አቋማቸውን አሳውቀዋል፡፡

ሽንፈቱን ተከትሎ መዶሻዎቹ በሊጉ 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን ከወረጅ ቀጠናውም የሶስት ነጥብ ርቀት ላይ ተቀምጠዋል፡

Advertisements