ድል / በጃፓን የሴቶች ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ መስከረም አሰፋ አሸናፊ ሆነች

ለ 38ኛ ጊዜ የተካሄደው እና በጃፓን ናጎያ በየአመቱ በወርሀ መጋቢት የሚካሄደው የሴቶች የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊቷ መስከረም አሰፋ አሸናፊ ሆናለች።

በጃፓን ከፍተኛ ህዝብ ከሚኖሩባቸው ከተሞች ውስጥ አንዷ የሆነችው ናጎያ የሚካሄደው አመታዊ የሴቶች የማራቶን ውድድር ዛሬ ተካሂዷል።

በውድድሩ ኢትዮጵያዊቷ መስከረም አሰፋ ከኋላ በመነሳት በድንቅ አጨራረስ አንደኛ ሆና ስታጠናቅቅ ተጠብቃ የነበረችው ኬኒያዊቷ ቫላሪ ጄሚሊ አይያቢ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

መስከረም አሸናፊ የሆነችበት ሰአት 2:21:45 ሲሆን ቫላሪ ጄሚሊ የገባችበት ሰአት ደግሞ 2:22:48 በሆነ ሰአት ነው።ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው ጃፓናዊቷ ዱቡታንቴ ሀናሚ 2:23:07 በመግባት የሶስተኛ ደረጃን አግኝታለች።

መስከረም 38ኛ ኪ ሜ ላይ ከኋላ በመነሳት ከፊቷ የነበረችው ኬኒያዊቷን አትሌት ቀድማ በማለፍ ያሸነፈችበት ሰአት የውድድሩ ሶስተኛ ፈጣኑ ሰአት ሆኖ ተመዝግቧል።

በዘንድሮው ውድድር ከ 20ሺ በላይ አትሌቶች ሲሳተፉ የተሳታፊዎቹን ቁጥር ከባለፉት አመታት ከ 2ሺ በላይ ጭማሪ አሳይቷል።

የውድድሩ የባለፉት ሁለት አመታት አሸናፊ የነበረችው ባህሬናዊቷ ኡኒስ ኪርዋ ስትሆን ያለፉት 37 ውድድሮችን ብዙውን ጊዜ ማሸነፍ የቻሉት ደግሞ ጃፓኖች ናቸው።

Advertisements