“ቼልሲ ባርሴሎናን በቻምፕየንስ ሊጉ አሸንፎ ለማለፍ ጥሩ እድል አለው” – ኦሊቬ ዥሩ

የፊታችን እሮብ በካምፕ ኑ ባርሴሎና ቼልሲን ከሚያስተናግድበት የቻምፕየንስ ሊጉ የመልስ ጨዋታ በፊት ኦሊቬ ዥሩ ቼልሲ ባርሴሎናን አሸንፎ ወደ ሩብ ፍፃሜ ለመቀላቀል ጥሩ እድል እንዳለው አሳውቋል።

ከሳምንት በፊት በስታንፎርድብሪጅ ሁለቱ ቡድኖች ያደረጉት ጨዋታ 1-1 የተለያዩ ሲሆን የመልሱን ጨዋታ ካደረጉ በኋላ ወደ ሩብ ፍፃሜ የሚያልፈው ቡድን ይለያል።

ቼልሲዎች በሜዳቸው ያደረጉት ጨዋታ በዊሊያን ጎል መሪ መሆን ቢችሉም ሊዮ ሜሲ ለባርሴሎናዎች ከሜዳቸው ውጪ አስፈላጊ የሆነውን ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ እንዳደረገ ይታወሳል።

የመልሱ ጨዋታ ባርሴሎና በሜዳው የሚያደርግ በመሆኑ የተሻለ እድል እንዳለው ቢታሰብም የቼልሲ አጥቂው ኦሊቬ ዥሩ በበኩሉ ቡድናቸው ባርሴሎናን አሸንፎ የማለፍ ጥሩ እድል እንዳለው አሳውቋል።

“ወደ ሩብ ፍፃሜው ለመቀላቀል ጥሩ እድል እንዳለን አስባለው።ጠንካራ ጨዋታ እንደሆነ እናውቃለን ነገርግን በቡድናችን ጥራት እምነት አለን።”ሲል ተናግሯል።

ከእንግሊዞች ሲቲ እና ሊቨርፑል የሩብ ፍፃሜውን መቀላቀላቸው ያረጋገጡ ሲሆን ቶተንሀሞች ደግሞ በጁቬንቱስ ተሸንፈው ወድቀዋል።

ማን ዩናይትድ እና ቼልሲ በበኩላቸው ማክሰኞ እና እሮብ ከ ሲቪያ እና ከ ባርሴሎና ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ወደ ሩብ ፍፃሜ የማለፍ እጣ ፋንታቸውን የሚለዩ ይሆናል።

Advertisements