“ፍራንክ ዲቦር በፕሪምየር ሊጉ ታሪክ ደካማው አሰልጣኝ ነው” – ሆዜ ሞሪንሆ

የማንችስተር ዩናይትዱ ኃለቃ ጆዜ ሞሪንሆ ከቀድሞው የክሪስታል ፓላስ አሰልጣኝ ፍራንክ ዲቦር ወጣቱን አጥቂ ማርከስ ራሽፎርድን አስመልክቶ የደረሰባቸውን ወቀሳ ተከትሎ በሰጡት ምላሽ “በሊጉ ታሪክ ከታየው ደካማ አሰልጣኝ የመጣ የማይረባ አስተያየት” ሲሉ አጣጥለውታል፡፡

ፖርቱጋላዊው ቅዳሜ ከሰዓት በተካሄደው የላንክሻየር ደርቢ ወጣቱን አጥቂ ከ2018 አዲስ አመት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የቋሚ ተሰላፊነት ዕድል የሰጡት ሲሆን ተጫዋቹም ሁለቱን የማሸነፊያ ጎሎች በማስቆጠር ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን አስመስክሯል፡፡

ለቢቲ ስፖርት በተንታኝነት እየሰራ የሚገኘው ሆላንዳዊ የቀድሞ ኮከብ ዴቦር ጨዋታውን ተከትሎ በሰጠው አስተያየት ወጣቱን ራሽፎርድን አድንቆ ተጫዋቹ በአሰልጣኝ ሞሪንሆ መሰልጠኑን ግን “አሳዛኝ” ሲል ገልጾታል ፤ ዴቦር አክሎም “ተጫዋቹ ወጣት በመሆኑ አንድ ወይም ሁለት ጨዋታዎች ላይ ስህተቶችን ሊሰራ ይችላል፡፡ በአሰልጣኝ ሞሪንሆ ስር ግን የሚፈለገው ውጤት ስለሆነ በጥቃቅን ስህተቶች ተጫዋቾች ዳግመኛ ዕድልን ሲያገኙ አይታይም፡፡መረሳት የሌለበት ግን እንግሊዛዊው ገና የ20 አመት ታዳጊ መሆኑ ነው” ብሏል፡፡

ይህን የዴቦር አስተያየት ተከትሎ ምላሻቸውን የሰጡት ጆዜ “አንዳንድ ነገሮችን አንብቤአለሁ ፤ ይህም በሊጉ ታሪክ ከታዩ ደካማ አሰልጣኞች ግንባር ቀደም የሆነውን የዴቦርን አስተያየት ነው፡፡ ዴቦር እኔ ማሸነፍ ብቻ ስለምፈልግ ራሽፎርድን እንዳልተጠቀምኩበት ተናግሯል፡፡ እሱ የራሽፎርድ አሰልጣኝ ቢሆን ግነ ተጫዋቹ ይሄን ጊዜ ጠፍቶ ነበር፡፡ ምክንያቱም እሱ ሁል ጊዜ ይሸነፋልና”

“ለሚገባው ሰው ክብርን እሰጣለሁ፡፡ ለቀድሞው የዩናይትድ አሰልጣኝ ቫንሃል ክብር አለኝ ፤ ራሽፎርድን በመጀመሪያ ወደቡድኑ ያመጡት እሳቸው ናቸው፡፡ ሆኖም ባለፉት ሁለት አመታት ተጫዋቹ በኔ አመራር ስር ያደረገውን የጨዋታ ብዛት ብትመለከቱ በክለቡ ብዙ የጨዋታ ዕድልን ከሰጠዋቸው 5 ተጫዋቾች አንዱ መሆኑን ትረዳላችሁ ” በማለት ጆዜ ራሽፎርድን አስመልክቶ የሚደርስባቸው ትችት በመረጃ ያልተደገፈ እንደሆነ ለመጠቆም ሞክረዋል፡፡

Advertisements