ስኬት / አል አህሊ የ2017/2018 የግብፅ ፕሪምየርሊግን በማሸነፍ ለ 40ኛ ጊዜ ተሞሾረ

በአፍሪካ የክለቦች ውድድር እንዲሁም በግብፅ ፕሪምየርሊግ የጎላ ታሪክ እያስመዘገበ የሚገኘው አህሊ የ2017/2018 የግብፅ ፕሪምየርሊግን ለ 40ኛ ጊዜ አሸናፊ መሆኑን ስድስት ጨዋታዎች እየቀሩት አረጋግጧል።

የአንድ ክለብ የበላይነት ጎልቶ የሚታይበት የግብፅ ፕሪምየርሊግ ልማደኛው አል አህሊ ለ አራት ተከታታይ አመታት የዋንጫ ባለቤት መሆኑን አረጋግጧል።

ቡድኑ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቻምፕየንስ ሊግ ላይ የበላይ በመሆን ስምንት ጊዜ ዋንጫ በማንሳት ከፍ ብሎ ተቀምጧል።

ይህ የአህጉራዊ ስኬቱ ደግሞ ከሀገሩ ባላንጣው ቡድን ከሆነው ዛማሌክ በ ሶስት ዋንጫዎች የተሻለ በመሆኑ ክለቡ በርግጥም ግብፃዊያን በአፍሪካ የክለቦች ውድድር ጭምር ስማቸው በተደጋጋሚ እንዲነሳ ማድረግ ችሏል።

ዋንጫ ያልሰለቸው አህሊ የሀገር ውስጥ ውድድር ላይም አይነኬ ሆኗል።እሁድ ENPPI 1-0 ካሸነፈ በኋላ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን አንድ ነጥብ ብቻ ቀርቶት የነበረ ቢሆንም ሰኞ ምሽት ላይ አል ማስሪ ለ ኢንታግ ኤል ሀርቢ አቻ በመለያየታቸው የዋንጫ ባለቤት መሆኑን አረጋግጧል።

28 ጨዋታዎችን ተጫውቶ 75 ተጥቦችን የሰበሰቡት “ቀያይ ሰይጣኖች” ከተከታዮቹ ኢስማይሊ እና ዛማሌክ ያለው የነጥብ ልዩነት በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ተከታዮቹ ሊደርሱባቸው የማይችሉ በመሆኑ በጊዜ ዋንጫውን ለአህሊ አስረክበዋል።

በቀሪዎቹ ጨዋታዎችም ቀያይ ሰይጣኖቹ ትኩረታቸውን ወደ አፍሪካ ቻምፕየንስ ሊግ በማድረግ የሀገር ውስጥ ውድድራቸውን በወጣት እና በቂ የመሰለፍ እድል ባላገኙ ተጫዋቾች እንደሚጫወቱ ይጠበቃል።

በቻምፕየንስ ሊግ የጋቦኑን ሲ ኤፍ ሞኖናን በመጀመሪያው ጨዋታ ላይ 4-0 በማሸነፋቸው ወደ ምድብ ድልድሉ አንድ እግራቸውን ማስገባት ችለዋል።

Advertisements