ድል / ወላይታ ዲቻ በመለያ ምት የግብፁን ሀያል ዛማሊክ በመርታት በአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ወደ ቀጣዩ ዙር ተቀላቀለ

ምስል : ከማህበራዊ ሚዲያ ገፅ የተገኘ

ወላይታ ዲቻ በአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የግብፁን ሀያል ዛማሊክ በመለያ ምት 4-3 በመርታት ወደ ቀጣዩ ዙር መቀላቀል ችሏል።

ከቀናት በፊት በሜዳው የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያ የግብፁን ክለብ 2-1 በመርታት ወደካይሮ ያመራው የአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሀ ስብስብ በዛሬው የመልስ ጨዋታ በ 2-1 ውጤት ጨዋታውን ቢጨርስም በድምር ውጤት ሁለቱ ቡድኖች 3-3 ሆነው በማጠናቀቃቸው በተሰጠው የመለያ ምት ተጋጣሚውን መርታት ችሏል።

የጦና ንቦቹ በአልሰላም ስታዲየም በተደረገው የምሽቱ ጨዋታ ባለሜዳው ዛማሊክ አጥቅቶ በመጫወት ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም እንግዳዎቹ ዲቻዎች ግባቸውን ሳያስደፍሩ ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል።

ዲቻዎቹ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላም ተስፋ ባለመቁረጥ ያደረጉት ከፍተኛ ጥረት የኋላ ኋላ ጥሩ አጋጣሚን ፈጥሮላቸው በመለያ ምት የ 4-3 ድልን እንዲቀናጁና ቀጣዩን ዙር እንዲቀላቀሉ ትልቅ እገዛ አድርጎላቸዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ በትናንትናው ዕለት ከአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ በመሰናበቱ ወደ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ እንዲመጣ ከመደረጉ ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ በሁለት ክለቦች የምትወከል ይሆናል። 

ዲቻ በመጪው ረቡዕ መጋቢት ካይሮ ላይ በሚወጣው የሁለተኛ ዙር የጥሎ ማለፍ ድልድል ከቻምፒየንስ ሊግ ከተሰናበቱ 16 ቡድኖች አንዱን የሚያገኝ ሲሆን በደርሶ መልስ ጨዋታ ውጤት አላፊ መሆን ከቻለ ወደ ምድብ ድልድል ይቀላቀላል።

Advertisements