የሊቨርፑሉ አምበል ሄንደርሰን የሳላህና የስዋሬዝ ንፅፅር አላስደሰተውም

መሐመድ ሳላህ በዋትፎርድ ላይ ያስቆጠራቸው አራት ግቦች ስዋሬዝ በሊቨርፑል ቆይታው የፈፀማቸውን ጀብዱዎች እንዲታወሱ ያደረገ ቢሆንም ነገር ግን ይህ ንፅፅር ጆርዳን ሄንደርሰንን አላስደሰተውም።

ልዊስ ስዋሬዝ የብሬንዳን ሮጀርሱ ቡድን ለእንግሊዝ ፕሪሚየር የዋንጫ በቅርብ ርቀት እንዲፎካከር ማድረግ በቻለበት 2013-14 የውድድር ዘመን ጆርዳን ሄንደርሰን ከኡራጓዊው ኮከብ ጋር አብሮ ተጫውቷል።

ብዙዎችን በሚያስማማ ሁኔታም በታህሳስ 2013 ሊቨርፑል ኖርዊች ሲቲን 5ለ1 ሲረታ ስዋሬዝ ያሳየው ድንቅ ብቃት ሳላህ በሳምንቱ መጨረሻ ካሳየው ብቃት ጋር ለንፅፅር የሚቀርብ ነበር።

“ምርጡ ማን ነው? እንደዚህ ዓይነት ነገር አትጠይቁኝ።” ሲል ሄንደርሰን ስለሁለቱ የቀድሞው እና አዲሱ የአንፊልድ ጀግኖች ንፅፅር በምሬት ተናግሯል።

“ሁለቱም እጅግ ድንቅ ናቸው። እናም ሁለቱን ልታነፃፅራቸው አትችልም።

“ሁለቱ ይተለያዩ ተጫዋቾች ናቸው። ሁለቱም በርካታ ግቦችን እንደሚያስቆጥሩ እና ከኳስ ውጪም ጠንክረው እንደሚሰሩ አውቃለሁ። ነገር ግን ያን ማነፃፀር በጣም አስቸጋሪ ነው። ሁለቱም በየግላቸው በጣም ጥሩዎች ናቸው።

“ልዊስ ወደባርሴሎና በማምራትም በጣም ጥሩ እየሰራ ይገኛል። እሱ እኔ አብሬው መጫወት የምፈልገው አስደናቂ ተጫዋች ነው። ነገር ግን የሞ ይህ የውድድር ዘመን እጅግ ፈፅሞ የማይታመን ነበር።

“ይህንንም በየሳምንቱ እያደረገው ይገኛል። በመልበሻ ክፍል ውስጥም ሆነ በሁሉ ቦታ ጥሩ ልጅ ነው። እሱ በቡድናችን ውስጥ በመገኘቱም ከፍ ያለ ነገር ጨምሮልናል።” በማለት የቀዮቹ አማካኙ ሄንደርሰን ተናግሯል።

ሳላህ በዚህ የውድድር ዘመን ለመርሲሳይዱ ክለብ በሁሉም ውድድሮች ላይ በአጠቃላይ 36 አስደናቂ ግቦችን ከመረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።

Advertisements