የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና የኤፍኤ ዋንጫ የሳምንቱ ምርጥ ቡድን

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ እና የኤፍኤ ዋንጫ ውድድሮች ተሰባጥረው በተካሄዱበት የሳምንቱ መጨረሻ ጨዋታ መርሃግብሮች ለክለቦቻቸው ውጤታማነት ከፍ ያለ ብቃታቸውን አውጥተው መጠቀመም የቻሉ ምርጥ 11 ተጫዋቾችን እና አሰልጣኞች የተካተቱባት የሳምንቱ ምርጥ ቡድን የሚከተለውን ይመስላል።

ክርስቲያን ዋልተን (ዊጋን አትሌቲክ)

የ22 ዓመቱ ግብ ጠባቂ ከብራይተን በውሰት የመጣ ተጫዋች ሲሆን ይህ አምስተኛው የውሰት ቆይታው ነው። ምንም እንኳ ዊጋን አትሌቲክ በኤፍኤ ዋንጫ ጨዋታው ሽንፈት ቢደርስበትም ዋልተን ግን ካጨናገፋቸው በርካታ የግብ ሙከራዎች መካከል የሳውዛምፕተኑ ማኖሎ ጋቢያዲኒ የመታውን የፍፁም ቅጣት ምት ድንቅ ነበር።

ሴዛር አዝፒሊኬታ (ቼልሲ)

ስፔናዊው ተጫዋች ወጥ እና አስደናቂ ብቃት እያሳየ የሚገኝ የቼልሲ ተከላካይ ነው። ክለቡ በኤፍኤ ዋንጫው ከሜዳው ውጪ ሌስተርን እንዲያሸንፍም የአምበልነት ሚናውን በሚገባ መወጣት ችሏል።

ጄምስ ቶምኪንስ (ክሪስታል ፓላስ)

የክሪስታል ፓላሱ የመኃል ተከላካይ አሁንም ለክለቡ ግብ አስቆጥሯል። ይሁን እንጂ ከዚህም በላይ ክለቡ የጉዳት ቀውስ ላይ በሚገኝበት በዚህ ወቅት በተከላካይ ክፍሉ ላይ ወጥ የሆነ አስትማማኝ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል።

ሴድሪች ሶአርስ (ሳውዛምፕተን)

የመስመር ተከላካዩ ለሳውዛምፕተን ተሰልፎ በተጫወተበት 88ኛ ጨዋታው የመጀመሪያውን ኤፍኤ ዋንጫ ግቡ በዊጋን አትሌቲክ ላይ አስቆጥሯል። ፓርቱጋላዊው ተጫዋች በክለቡ አሰቸጋሪ የውድድር ዘመንም ጥሩ ጨዋታ ማደረጉን ከመቀጠሉም ባሻገር ግቧን በአስደናቂ ሁኔታ ማስቆጠርም ችሏል።

ጆርዳን ኢቤ (ቦርንማውዝ)

ኢቤ በትልቅ የዝውውር ዋጋ ከሊቨርፑል ወደቦርንማውዝ ከተዛወረበት ጊዜ አንስቶ በክለቡ ያሳለፈው ጊዜ ቀላል የሚባል አልነበረም። ነገር ግን በክለቡ ላይ ያለው አስተዋፅኦ በየጊዜው እየተሻሻለ በመምጣት ዌስት ብሮምዊች አልቢዮንን ማሸነፍ በቻሉበት ወሳኝ ጨዋታ ከረጅም ርቀት በመታት ኳስ ክለቡን አቻ ያደረገች ግብ አስቆጥሯል።

ንጎሎ ካንቴ (ቼልሲ)

ካንቴ ወደሌስተር ሲቲ ሲመለስ ከቀድሞው ክለብ ደጋፊዎች ከፍተኛ የተቃውሞ ድምፅ ተሰምቶበታል። ነገር ግን ተጫዋቹ በሳምንቱ መጨረሻ በባርሴሎና የደረሰባቸውን ሽንፈት የሚያዘነጋ ጉልበትና ኃይለኛ ስሜት ያለው ብቃቱን በአማካኝ ስፍራ ላይ ማሳየት ከመቻሉም በላይ የማሸነፊያ ግብም ማመቻቸት ችሏል።

ኒማኒያ ማቲች (ማንችስተር ዩናይትድ)

ማቲች ብዙውን ጊዜ ግብ ሲያስቆጥር መመልከት አልተለመደ ይሆናል። ነገር ግን ዩናይትድ ብራይተንን ማሸነፍ እንዲችል ያስቻለችውን ግብ ያስቆጠረው ግን እሱ ነበር። ከዚህም በላይ ግን ሆዜ ሞሪንሆ እንዳሉት ባለው ከፍ ያለ “ስብዕና” ለሌሎች ተጫዋቾች ተምሳሌት መሆኑን ቀጥሎበታል።

ክርስቲያን ኤሪክሰን (ቶተንሃም ሆትስፐር)

ሃሪ ኬን ባልነበረበት ጨዋታ ግብ የማስቆጠሩ ሚኖ በሙሉ ያነጣጠረው ሁሉንም በሚያግባባ መልኩ በሁንግ-ሚን ሶን ላይ ነበር። ነገር ግን ክለቡ በኤፍኤ ዋንጫው ከሜዳው ውጪ ስዋንሲን እንዲያሸንፍ በማገዙ በኩል ከፍተኛ ክህሎትን በማሳየትና ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ ኤሪክሰን ትልቁን ሚና ተጫውቷል።

መሐመድ ሳላህ (ሊቨርፑል)

የሊቨርፑሉ የፊት ተጫዋች አሁንም አስደናቂ ግብ የማስቆጠር ሚናውን ቀጥሎበት ቀዮቹ ዋትፎርድን 5ለ0 ማሸነፍ በቻሉበት ጨዋታ አራት ግቦችን ከማስቆጠሩም በላይ አምስተኛዋ ግብ በፊርሚኖ አማካኝነት ስትቆጠር ግቧን ያመቻቸው እሱ ነበር። ተጫዋቹ አሁን ከዓለማችን ምርጥ ተጫዋቾች ጋር በመነፀፀር ላይም ይገኛል።

ሴንክ ቶሱን (ኤቨርተን)

ቱርካዊው ተጫዋች ያስቆጠራቸው ሁለት ግቦች በሶስት ጨዋታች ላይ ያሳቆጠራቸውን ግቦች አራት አድርሰውለታል። በመጨረሻ ተጫዋቹ ከዚህ ቀደም ክፍተት የነበረበትን የኤቨርተን የፊት ክፍል በማገዝ ከክለቡ ጋር መዋሃድ ችሏል።

ዊልፍሬድ ዛሃ (ክሪስታል ፓላስ)

ዛሃ ተሰልፎ በሚጫወትባቸው ጨዋታዎች ላይ ፓላሶች የማግባት ዕድል ይኖራቸዋል። እሱ በሚጫወትበት ጊዜም የክለቡ አጨዋወት ህይወት ይዘራበታል። ተጫዋቹ ይህን ያህል ተፅእኖ ማሳደር የሚችል ተጫዋች ነው። በሚገርም ሁኔታም እሱ ባለተጫወተባቸው ዘጠኝ ጨዋታዎች ላይ በሙሉ ሽንፈት ገጥሟቸዋል።

አሰልጣኝ: ማርክ ሂዩዝ (ሳውዛምፕተን)

Advertisements