ስንብት / ሬዲንግ ከክለቡ ዋና አሰልጣኝ ያፕ ስታም ጋር መለያየቱን አሳወቀ

የቀድሞ የማንችስተር ዩናይትድ ተጫዋች የነበረው ሆላንዳዊው ያፕ ስታም ከሬዲንግ የአሰልጣኝነት ሀላፊነቱ መነሳቱ ክለቡ አሳወቀ።

በእንግሊዝ ከፕሪምየር ሊጉ በመቀጠል በቻምፕየንስ ሺፑ ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው ሬዲንግ በደረጃ ሰንጠረዡ 20ኛ ላይ ተቀምጧል።

ከአራት ቡድኖች ብቻ ተሽሎ ከወራጆቹ ሳይርቅ የተቀመጠው ሬዲንግ የከፋ ውጤት ሳይመጣ አሰልጣኙን ማሰናበት ምርጫው አድርጓል።

ምንም እንኳን የክለቡ አብዛኛዎቹ ባለ አክሲዮኖች ቡድኑ ከገባበት የውጤት ቀውስ እንዲያገግም ለአሰልጣኙ እድል ቢሰጡትም ክለቡ ካለፉት 18 ጨዋታዎች ውስጥ አንድ ጊዜ ብቻ በማሸነፍ በተጨባጭ የታየ ለውጥ ባለመኖሩ የመጨረሻውን የስንብት ውሳኔ መወሰን ችለዋል።

አሰልጣኙ በተለይም በመጀመሪያ አመቱ ላይ ለሰራው ስራ ትልቅ ምስጋና በማቅረብ በቀሪዎቹ የአሰልጣኝነት ህይወቱ መልካም ነገር እንዲገጥመው ክለቡ ተመኝቶለታል።

እስከ አመቱ መጨረሻ ድረስም አዲስ አሰልጣኝ በመቅጠር ክለቡ ቀሪ የውድድር ጊዜውን ከወራጅ ቀጠና ርቆ ለማጠናቀቅ እንደሚሰሩ ነው የታወቀው።

Advertisements