ዣቢ አሎንሶ አምስት ዓመት ዘብጥያ የሚያስወርድ ክስ ተመሰረተበት

የቀድሞው የስፔን ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ዣቢ አሎንሶ በታክስ ማጭበርበር ወንጀል ለዓመታት ወህኒ ቤት የሚያስገባ ክስ ተመስርቶበታል።

የስፔና አቃቤ ህግ ባወጣው መግለጫ በቀድሞው የሊቨርፑል፣ ሪያል ማድሪድ እና ባየር ሙኒክ አማካኝ ተጫዋች ላይ የአምስት ዓመት እስር እና 4 ሚሊዮን ዩሮ ቅጣት እንዲጣልበት ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቧል።

ዛሬ (ረቡዕ) በወጣው የአቃቤ ህግ መግለጫ ባለፈው የውድድር ዘመን መጨረሻ እግርኳስ ያቆመው የ36 ዓመቱ የቀድሞ ተጫዋች ከ2010 እስከ 2012 ባሉት ዓመታት ለስፔን መንግስት ማስገባት የሚገባውን ግብር ሰውሯል የሚል ክስ መስርቶበታል።

አቃቤ ህግ በአሎንሶ የፋይናንስ አማካሪ ኢቫን ዛልዱአ አዝኩናኛ እና የሼል ኩባንያ አማካሪ አስተዳዳሪ የሆኑት ኢግናሲ ማስቴሮ ካሳኖቫ ላይም ተመሳሳይ ክስ መመስረቱን በመግለጫው ጨምሮ ገልፅዋል።

አሎንሶ በስፔን መንግስት የግብር ማጭበርበር በቅርብ ዓመታት ዒላማ ከሆኑ ከፍተኛ ስም ካላቸው ስፖርተኞች መካከል ብቸኛው ተጫዋች አይደለም። ሊዮኔል መሲ፣ ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ጆዤ ሞሪንሆም ባለፉት 12 ወራት በተማሳሳይ ጉዳይ ምርመራ ሲደረግባቸው ቆይተዋል።

በባርሴሎናው ኮከብ መሲ ላይ የታላለፈው የ21 ወራት የእስር ፍርድ ወደቅጣት ዝቅ እንዲል የተደረገውም ባለፈው ኃምሌ ወር ነበር።

Advertisements