የምስራቅ አፍሪካዎቹ ያንጋ እና ድቻ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ይፋጠጣሉ

በአፍሪካ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ አስደናቂ ጉዞ እያደረገ የሚገኘው ወላይታ ድቻ ወደ ምድብ ድልድሉ ለመግባት የመጨረሻውን ጨዋታ ከታንዛኒያው ያንጋ ጋር እንዲያደርግ  ተደለደለ።

ምሽት ላይ በወጣው ድልድል መሰረት በካፍ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወደ ምድብ ድልድሉ ውስጥ ለመግባት የሚደረጉት የመጨረሻ ተጋጣሚዎች ታውቀዋል።

ከቻምፕየንስ ሊግ ወደ ምድብ ድልድል መግባት ያልቻሉ ቡድኖች እንዲሁም በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወደ መጨረሻው ዙር ያለፉ ቡድኖች በድልድሉ ውስጥ ተካተዋል።

ዚማሞቱ እና ዛማሌክን በማሸነፍ ለዛሬው ድልድል የበቃው የኢትዮጵያው ወላይታ ድቻም  ከታንዛኒያው ያንግ አፍሪካ ጋር ተደልድሏል።

ያንጋ በታንዛኒያ ከፍተኛ ደጋፊ ያለው በመሆኑ ከድቻ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል።

የያንጋ የከተማው ደርቢ የሆነው ሲምባ ከዚህ ቀደም ያንግ አፍሪካ በሚያደርጋቸው የአፍሪካ ቻምፕየንስ ሊግ የሜዳው ጨዋታዎች ለተቃራኒ ቡድን በመደገፍ ይታወቃል።

ይህ ደግሞ ለወላይታ ድቻዎች ከሜዳቸው ውጪ ለሚያደርጉት ጨዋታ ሌላ የድጋፍ ሀይል ሊሆንላቸው እንደሚችል ይጠበቃል።

ድቻ ይህን የደርሶ መልስ ጨዋታ ማሸነፍ የሚችል ከሆነ ወደ ምድብ ድልድሉ መሳተፍ የሚችል ይሆናል።

ቡድኑ ዛማሌክን ካሸነፈ በኋላ ብዙዎቹ ትኩረት ያደረጉበት ሲሆን ወደ ሀገሩም ሲመለስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል።

ድቻ በመጀመሪያ ተሳትፎው እያስመዘገበ የሚገኘው ውጤት በተለይም የግብፁን ዛማሌክን አሸንፎ ማለፉ የሚደነቅ በመሆኑ ለቀጣዩ ጨዋታ የራሳቸው የራስ መተማመን ከፍ ስለሚያደርገው ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል።

ሙሉ ድልድሉን ከላይ ካለው ምስል ይመልከቱ