የ”ሲን-ቢን” ህግ በእግርኳስ ጨዋታ ላይ ጠቀሜት ይኖረው ይሆን?

ሲን-ቢን አንድ ተጫዋች ቢጫ ካርድ ሲመለከት ለተወሰኑ ደቂቃዎች ከሜዳ በመውጣት በጨዋታ ላይ እንዳይሳተፍ ነገር ግን የደቂቃዎች ቅጣቱን ሲጨርስ ተመልሶ ወደሜዳ እንዲገባ የሚደርግበት በረግቢ፣ በበረዶ ገና እና በሌሎችም ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ አገልግሎት ላይ የሚውል ጊዜያዊ የቅጣት ዓይነት ነው።

በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ጨዋታ ላይ ይህ ዓይነቱ ቅጣት ጨርሶ አይታወቅም። ነገር ግን ሲን-ቢን በእንግሊዝ እግርኳስ ለወደፊቱ “ተግባራዊነቱ እርግጥ እየሆነ በመምጣት ላይ እንደሚገኝ” የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ዋና የዳኞች ዋና ኃላፊ የሆኑት ኒል ባሪ ተናግረዋል።

የዓለም አቀፉ የእግርኳስ ማህበር ቦርድ አስቀድመው ሙከራ እንዲያደርጉት ለእንግሊዝ ብሄራዊ የእግርኳስ ማህበራት ፈቃድ መስጠቱን ተከትሎ በእንግሊዝ ኖቲንግሃምሻየር አከባቢ በሚገኙ የከተማዋ የሊግ ውድድሮች ላይ ተጫዋቾች ቢጫ ካርድ ሲመለከቱ ለ10 ደቂቃ በጨዋታው ላይ ያለመሳተፍ ቅጣት የሚያስተላልፈውን ይህን የሲን-ቢን ህግን ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል።

የዳኞች ሳምንትን በማስመልከት ለስካይ ስፖርት ቴሌቪዥን ጣቢያ የተናገሩት ባሪ እስከሁን የህጉ ተግባራዊነት አዎንታዊ ውጤት እያማጣ እንደሚገኝ ቢናገሩም ከፕሮፌሽናል ጨዋታዎች ይልቅ ለታዳጊዎች እግርኳስ ይበልጥ የተስማማ እንደሆነ ግን ተናግረዋል።

“ስራ ላይ መዋል መቻሉ እርግጥ እየሆነ የመጣ ይመስለኛል። እኛም እንደእግርኳስ ማህበር ለወደፊቱ ተግባራዊ እንደምናደርገው እርግጥ ነው።

“ባለፈው ዓመት ሲን-ቢንን በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ያደረጉ 32 ሊጎች ነበሩን። እናም አዎንታዊ ውጤት ነበረው። በሚቀጥለው የውድድር ዘመን የምንሞክርበትን የሊግ ቁጥር ከፍ እናደርጋለን። ስለዚህ በ2019/20 ቁጥሩን ከፍ የማድረግ ሃሳብ አለን።

“አሁን እየተወያየንበት የምንገኘው ሲን-ቢንን እስከየትኛው ሊግ ድረስ ተግባራዊ ልናደርገው እንደምንችል ነው። ጅማርዎቹ በጣም በጣም አዎንታዊ ነበሩ። እናም ሰዎች ሊሰራ እንደሚችል ተረድተዋል። እኛም ቀስ በቀስ ተግባራዊ ልናደርገው ይገባል። ያለጥርጥርም በቀጣዩ ዓመት በታዳጊዎች እግርኳስ ላይ ስራ ላይ ይውላል።” በማለት ባሪ ገልፀዋል።

ባሪ ሲን-ቢንን ማስተዋወቅ በጨዋታ ላይ የሚፈጠርን ውዝግብ ይቀንሳል ብለው እንደሚያምኑ ገልፀው አሃዞች እንደሚያረጋግጡትም ተጫዋቾች ቡድናቸውን ሊጎዳ እንደሚችል ሲያስቡት ለድርጊታቸው ይበልጥ ተጠያቂነትን እንደሚወስዱም ጨምረው ተናግረዋል።

ባሪ ይህን አስመልክተው ሲናገሩም “የዳኛውን ስራ የሚያቀል እና ሰዎች ለድርጊቶቻቸው ተጠያቂናት እንዲወስዱ የሚያግዝ ማንኛውንም ነገር ስራ ላይ ልናውል እንችላለን። ይህ ደግሞ የጨዋታን ገፅታ እንደሚያሻሽል ተስፋ አለን። በ32ቱ ሊጎች ላይ ባደረግነው ሙከራ በጨዋታ ላይ የሚፈጠርን አለመግባባት በ38 በመቶ እንዲቀንስ አድርጎታል። ይህ ሁሉ የሆነው ደግሞ በአቻ ግፊት ይመስለኛል።

“በዳኛ ውሳኔ የሲን-ቢን ቅጣት ላይ የምገኝ ብሆን እና የ10 ደቂቃ ቅጣት የተጣለብኝ ብሆን፣ በድርጊቴ የቡድን አጋሮቼ ፈፅሞ ደስተኛ አይሆኑም። ስለዚህ የሚፈጠረውን አለምግባባት የቀነሰው ይህ ይመስለኛል።” ብለዋል።

ይሁን እንጂ በተቃራኒው ከዚህ ቀደም የፕሪሚየር ሊግ ዳኛ የነበሩት ዴርሞት ጋለግኸር የሲን-ቢን ፓሊሲ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ተናግረው አዲሱ ህግ በወቅታዊ ጨዋታዎች ላይ በትክክል ይሰራል ብለው አያሳቡም።

“አንዳንድ ዳኞች ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ያስባሉ። አንዳንዶች የሚያስቡት ደግሞ በተቃራኒው ነው ። ነገር ግን በጣም ከባድ ፖሊሲ ነው። ምክኒያቱም አንድን ተጫዋች የ10 ደቂቃ ሌላውንም እንዲሁ 10 ደቂቃ የሲን-ቢን ቅጣት ስቀጣቸው ያን ጊዜ አራተኛ ዳኛ የሚባል ነገር አይኖርም።

“ስለዚህ የአራተኛ ዳኞች የሜዳ ላይ ሚና በእጅጉ አስቸጋሪ ይሆናል። ጥሩ ሃሳብ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አሁን ላይ መተግበሩን ግን እርግጠኛ አይደለሁም።” በማለት ጋላግኸር ተናግረዋል።

Advertisements