የተረጋገጠ/ ዝላታን ኢብራሒሞቪች ለአሜሪካው ኤል ኤ ጋላክሲ ፈረመ

​ግዙፉ ስውዲናዊ የፊት አጥቂ ዝላታን ኢብራሒሞቪች በማንችስተር ዩናይትድ የነበረውን ቆይታ በመቋጨት ወደአሜሪካው ሎስ አንጀለስ ጋላክሲ ተዘዋውሯል፡፡

የ36 አመቱ የቀድሞ የአያክስ አምስተርዳም ፣ ጁቬንቱስ ፣ኢንተር ሚላን ፣ኤሲ ሚላን ፣ ባርሴሎናና ፒኤስጂ ኮከብ ዝላታን ባለፈው የውድድር ዘመን ማንችስተር ዩናይትድን ተቀላቅሎ የጉልበት ጉዳትን እስካስተናገደበት ጊዜ ድረስ 28 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን ከጉዳት ተመልሶ ሰባት ጨዋታዎችን ለክለቡ ካደረገ በኋላ ጉዳቱ በድጋሚ አገርሽቶበት ቆይቷል፡፡

ግዙፉ ኮከብ ወደአሜሪካው ክለብ ለማምራት ከክለቡ አለቃ ጆዜ ሞሪንሆ ፈቃድ እንዳገኘ ለረጅም ጊዜያት ሲነገር የቆየ ሲሆን በመጨረሻም ዝውውሩ እውን ሆኖ በሜጀር ሊጉ የመጫወት ዕድልን አግኝቷል፡፡

የአሜሪካ ሜጀር ሊግ የታላላቅ የእግር ኳስ ከዋክብት የመጨረሻ የጨዋታ ዘመን ማገባደጃ መሆን ከጀመረ ሰንበትበት ያለ ሲሆን ከዚህ ቀደም በዴቪድ ቤካም የተጀመረው ጉዞ ቀጥሎ ሪካርዶ ካካ ፣ ቴዬሪ ሄንሪ ፣ ፍራንክ ላምፓርድ ፣አንድሪያ ፒርሎና መሰል ተጫዋቾች ማረፊያ መሆኑ ይታወሳል፡፡

Advertisements