“የደረሰብኝ የዘረኝነት ጥቃት የእግር ኳስ ህልሜን አምክኖታል” – የቀድሞው የቼልሲ ተጫዋች

የቀድሞው የቼልሲ ተጫዋች በ 1980ዎቹ የወጣት እድሜው በስታምፎርድ ብሪጅ የደረሰበትን እና የእግር ኳስ ህይወቱን ያበላሸበትን የዘረኝነት ጥቃት አስታወሶ ተናግሯል፡፡  

ስሙን እንዲገለፅ ያልፈለገው ተጫዋቹ ከስካይ ስፖርት ጋር ባደረገው ቆይታ ሁሌም ሊባል በሚችል ደረጃ “ሊስትሮው” እየተባለ ዝቅ ተደርጎ እስከመጠራት የዘለቀ የዘረኝነት ትንኮሳ ይፈፀምበት እንደነበር ይፋ አድርጓል፡፡ 

የቀድሞው ተጫዋች ከ 13 አመቱ አንስቶ እስከ 18 አመት የወጣትነት ጊዜው በስታምፎርድ ብሪጁ ክለብ የደረሰበትን መገለል ሲያስረዳም ሁኔታውን ለባለቤቱ ጭምር እንዳልነገራት ገልጿል፡፡  

ባሳለፍነው ጥር ወር ላይ ሶስት የቀድሞ የቼልሲ ወጣት ቡድን አባላት ተመሳሳይ የዘረኝነት ድርጊት እንደተፈፀመባቸው መናገራቸው የማይረሳ ሲሆን ስሙ ያልተገለፀው የአሁኑ የጥቃቱ ተጎጂም ድርጊቱ ህይወቱን እንዳመሰቃቀለበት እና ብዙ ፈተናዎችን እንደተጋፈጠ አብራርቷል፡፡

አሁን በ50ኛ አመት እድሜው ላይ የሚገኘው የቀድሞው ተጫዋች እንደሚለው ከሆነ በክለቡ የሚደርስበት የዘረኝነት ጥቃት መንፈሱን ይጎዳው ስለነበር ሰበብ እየፈለገ ከልምምድ እንደሚቀርና በዚህ ምክንያትም ከቼልሲ ጋር ያለው የውል ስምምነት ሲፈርስ የፕሮፌሽናልነት የእግር ኳስ ህልሙም በዛው አብቅቶለታል፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት እየሰጡ የተለያዩ አካላትም ከ 30 እና 40 ዓመታት በፊት ለተፈፀመው ጥፋት የቼልሲ እግር ኳስ ክለብ በይፋ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበት እየተናገሩ ሲሆን ክለቡ በቃለ አቀባዩ ዙሪያ በሰጠው መግለጫም በድርጊቱ የተጎዱ አካላት ሊደረግላቸው ወይም ሊረዱበት በሚገባ መንገድ ሁሉ ለማገዝና ለመተባበር ፍቃደኛ መሆኑ አስታውቋል፡፡

የምዕራብ ለንደኑን ክለብ በተመለከተ ከአመታት በፊት ይፋ የሆነ ሌላ መረጃ የክለቡ የመጀመሪያው ጥቁር ተጫዋች ፓል ካኖቪል የአራት አመታት ከግማሽ የስታምፎርድ ብሪጅ ቆይታ በዘረኝነት ጥቃት የታጀበ እንደነበር ይፋ ማድረጉ አይረሳም፡፡    

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በቼልሲ ዙሪያ ይፋ የሚደረገውን የዘረኝነት ጥቃት የተመለከተ መረጃ ለብዙዎች አስገራሚ የሚያደርገው ክለቡ ከላይቤሪያዊው ጆርጅ ዌሀ አንስቶ እስከ ቅርብ ጊዜዎቹ ዲዲየር ድሮግባ፣ ማይክል ኢሴይን እና ሰለሞን ካሉ ድረስ በአፍሪካ ተጫዋቾች ስኬታማ መሆን መቻሉ ነው፡፡

Advertisements