የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ የሆነው ሮበርት ኦዶንግካራ ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውጪ ሆነ

ዩጋንዳዊው የቅ/ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ የሆነው ሮበርት ኦዶንግካራ በጉዳት ከዩጋንዳ ብሐራዊ ቡድን ውጪ ሆነ።

የፈረሰኞቹ ግብ ጠባቂ በመሆን ላለፉት ረጅም አመታት እየተጫወተ ያለው ሮበርት ኦዶንግካራ ለቡድኑ የፕሪምየርሉጉ ውጤታማ አመታት በትልቁ ስሙ ይጠቀሳል።

ተጫዋቹ በተደጋጋሚ ጊዜ የፕሪምየርሊጉ ኮከብ ግብ ጠባቂ በመሆን በግሉም ይሁን ከቡድኑ ጋር ስኬታማ ጉዞን አድርጓል።

በዘንድሮው የቅ/ጊዮርጊስ ቡድን አባልም ሆኖ እየተጫወተ የሚገኘው ሮበርት ምንም እንኳን ቡድኑ በሀገር ውስጥም ይሁን በአፍሪካ ቻምፕየንስ ሊግ ላይ ደካማ ጉዞን ቢያደርግም በግሉ አቋሙ ወርዷል ብሎ መናገር አይቻልም።

ቅ/ጊዮርጊስ ወደ ሀዋሳ አቅንቶ ያደረገው የኢትዮጵያ ፕሪምየርሊግ ጨዋታ ላይ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው ግብ ጠባቂ በአፍሪካ ቻምፕየንስ ሊጉ ላይ ላይደርስ እንደሚችል ተነገሮ ነበር።

ነገርግን ተጫዋቹ በፍጥነት በማገገም በሁለቱም የቻምፕየንስ ሊጉ ጨዋታ ላይ ተሰልፎ ተጫውቷል።

ፈረሰኞቹ ከካምፓላ ተሸንፈው ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ዩጋንዳዎች ላለባቸው የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ምክንያት ኦዶንግካራ ሳይመጣ ቀርቷል።

“ክሬንሶቹ” ከሳኦቶሜ እና ማላዊ ጋር ላለባቸው የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች ላይ ወደ ቡድኑ ካምፕ ለልምምድ መቀላቀል ችሎ ነበር።

ነገርግን ቀደም ብሎ አጋጥሞት በነበረው የጉልበት ጉዳት ምክንያት የብሔራዊ ቡድኑ ሀኪሞች እረፍት እንዲያደርግ ከቡድኑ ውጪ እንዲሆን አድርገዋል።

በምትኩም የኬሲሲኤው ግብ ጠባቂ የሆነው  ቻርለስ ሉክዋጎ ወደ ብሄራዊ ቡድኑ እንዲቀላቀል ጥሪ ቀርቦለታል።

Advertisements