ኢማኑኤል አሙኒኬ ከሱዳኑ ኤል ካርቱም የአሰልጣኝነት ሀላፊነቱ በጋራ ስምምነት ተለያየ

​የቀድሞ የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ምርጥ ተጫዋች የነበረው ከባለፈው ህዳር ወር ጀምሮ የሱዳኑን ኤል ካርቱምን በዋና አሰልጣኝነት ሲያሰለጥን የነበረው ኢማኑኤል አሙኒኬ ከቡድኑ ጋር በጋራ ስምምነት ተለያየ።

የናይጄሪያ ከ 17 እና ከ 20 አመት በታች ማሰልጠን ችሎ የነበረው አሙኒኬ ወደ ሱዳን በማቅናት ኤል ካርቱም የተባለውን ክለብ ሲያሰለጥን ቆይቷል።

አሰልጣኙ በክለቡ የቆየባቸው አጭር ወራት ቢሆኑም መልካም ጅማሮ በማድረግ ለውጥ መፍጠር ችሎ ነበር።

ነገርግን የሚከፈለው ደሞዝ ለሱዳኑ ክለብ ፈተና በመሆኑ ላለፉት ሁለት ወራት ምንም አይነት ደሞዝ ሳይከፈለው ቆይቷል።

በጉዳዩ ዙሪያ ላይ ከክለቡ ባለቤት ማኦሞን ባሂር ጋር ባለፈው ማክሰኞ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመወያየት የተቀመጠው አሙኒኬ ክለቡ በገንዘብ እጥረት ደሞዙን ለመክፈል እንደተቸገረ ነግረውት እንዲለያዩ በሩን ክፍት አድርጎለታል።

በዚህም ምክንያት ከአራት ወራት ቆይታ በኋላ ኢማኑኤል አሙኒኬ ከሱዳኑ ክለብ ጋር በጋራ ስምምነት ለመለያየት ችሏል።

አሙኒኬ ቡድኑ አዲስ ባደገው አህሊ ሞሮው 3-1 ከተሸነፈ በኋላ እንደተባረረ የተናፈሰው መረጃም ከእውነት የራቀ መሆኑን አስረድቷል።

“ለሁለት ወራት ደሞዝ ካልተከፈለኝ በኋላ ከክለቡ ዳይሬክተር ጋር ማክሰኞ ለታ ውይይት አድርገናል።እሱም ክለቡ በገንዘብ እጦት መቸገራቸውን አስረድቶኛል።

“ደሞዜንም ለመክፈል እንደሚቸገሩ ስለነገሩኝ በጋራ ስምምነት ተለያይተናል።” በማለት ከክለቡ የለቀቀው ተባሮ ሳይሆን ደሞዙን ሊከፍሉት ስላልቻሉ እንደሆነ አሳውቋል።

Advertisements