የአርሰናል ተጫዋቾች ኮንትራት መቼ ይጠናቀቃል?

ከሁለት አስርት ዓመታ የክለቡ ቆይታ በኋላ በውጤት ማጣት ምክኒያት በስንብት አደጋ ውስጥ በሚገኙት አርሰን ቬንገር የሚሰለጥኑት የመድፈኞቹ ተጫዋቾች ኮንትራት እስከመቼ ይዘልቃል? ተከታዩ ፅሁፍ ሁሉም የአርሰናል የመጀመሪያው ቡድን ተጫዋቾች ከክለቡ ጋር ያላቸው ኮንትራት የሚጠናቀቅበትን ገዜ በአንድ በዝርዝር ያስቃኘናል።

ጃክ ዊልሼር – 2018

እንግሊዛዊው ተጫዋች በአሁኑ ጊዜ በክለቡ ለመቆየት የሚያስችለውን ኮንትራት ስለሚያራዝመበት ሁኔታ ከአርሰናል ጋር እየተነጋገረ ይገኛል።

ዊልሼር ከታዲገነት እድሜው አንስቶ በተጫወተበት ክለብ የመቆየት ፍላጎት ያለው ቢሆንም የደመወዝ ክፍያውን እንዲቀንስ የሚያደረገውን ከክለቡ የቀረበለትን አዲስ የስምምነት ጥያቄ ግን ሳይቀበል ቀርቷል።

አርሰን ቬንገርም ዊልሼርን የማቆየት ፍላጎት እንዳለቸው ነገር ግን የወደፊት እጣ ፈንታው ገና በእንጥልጥል ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሳንቲ ካዛሮል – 2018

ስፔናዊው ተጫዋች ለ10 ጊዜያት ያህል የቀዶ ጥገና እንዲያደርግ ምክኒያት በሆነው መጥፎ የሚባል የተረከዝ ጉዳት ከዓመታት በላይ ከሜዳ እንደራቀ ይገኛል።

ተጫዋቹ ይህ የውድድር ዘመን ሲጠናቀቅ ስምምነቱ የሚጠናቀቅ እንደመሆኑ አርሰናል ተጫዋቹን በነፃ ለመልቀቅ ይገደዳል።

በጥር ወር ለካዛሮላ አዲስ የስምምነት ጥያቄ ይቀርብለት እንደሆነ ጥያቄ የቀረባላቸው ቬንገር ስምምነቱ “መሰረት የሚያደረገው በሚያገኘው ህክምና ላይ” እንደሆነ ተናግረው “ይህንንም እስከውድድር ዘመኑ ድረስ የምንከታተለው ይሆናል። ሳንቲ ወደጥሩ አቋሙ የሚመለስ ከሆነም ያን ጊዜ አዎ ማሰገፈረሙን የምናስብበት ጉዳይ ይሆናል።” ብለው ነበር።

ፐር ሜርትሳከር – 2018

ጀርመናዊው ተከላካይ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ እግርኳስ መጫወት እንደሚያቆም አስቀድሞ አሳውቋል።

በመጪው ክረምትም በይፋ አዲሱ የአርሰናል የማሰልጠኛ ተቋሙ አሰልጣኝም ይሆናል።

ዮል ካምፕቤል – 2018

ኮስታ ሪካዊው የፊት ተጫዋች በክረምቱ አርሰናልን ይለቃል።

ተጫዋቹ በአሁኑ ጊዜ በስፔኑ ክለብ ሪያል ቤቲስ በውሰት እየተጫወተ የሚገኝ ሲሆን ከአርሰናል ጋር ያለው ስምምነቱ ሲያበቃም በቋሚነት በስፔን መጫወት ፍላጎት እንዳለውም ገልፅዋል።

አሮን ራምሴ – 2019

አርሰናል ከዌልሳዊው ተጫዋች ጋር የኮንትራት ስምምነቱን ለማራዘም ጉዳይ እየተነጋገረ ቢገኝም እስካሁን ግን የተጫዋቹን ኮንትራት አላራዘመም።

ራምሴ ከእንግሊዝ ወጥቶ የመጫወት ፍላጎት እንዳለው አስተያየቶች እየተሰጡ ቢገኙም አርሰናል በክረምቱ ስምምነቱ የአንድ ዓመት ቀሪ ጊዜ ብቻ በሚቀረው የ27 ዓመቱ ተጫዋች ጉዳይ ውሳኔ የማሳለፍ ችግር ውስጥ የሚገባም ይሆናል።

አርሰን ቬንገር ግን ራምሴ በክለቡ እንዲቆይ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ገልፀዋል።

ዳኒ ዌልቤክ – 2019

አርሰናል ዌልቤክን በክለቡ የማቆየት ፍላጎት እንዳለው ቢገልፅም ነገር ግን የፊት ተጫዋቹ በመጪው ክረምት ለሌላ ክለብ ተላልፎ ሊሸጥ እንደሚችል ይጠበቃል።

ተጫዋቹ በአርሰናል ከአሌክሳንደር ላካዜቴ እና ፒየር ኤመሪክ-አውባምያንግ ቀጥሎ የሚመረጥ ተጫዋች በመሆኑ በክለቡ አዲስ ኮንታራት የመፈረሙ ነገር አናሳ ነው።

ናቾ ሞንሪል – 2019

ስፔናዊው ተጫዋች ከማላጋ ወደአርሰናል የተዛወረው በ2013 የነበረ ሲሆን፣ በኤመራትስም ጥሩ ጊዜን አሳልፏል።

ያለምንም ጥርጥርም አርሰናል ተጫዋቹን ለማቆየት ፍላጎት ይኖረዋል።

ፒተር ቼክ – 2019

የካበተ ልምድ ያለው ግብ ጠባቂ ከቼልሲ አርሰናልን የተቀላቀለው በ2015 ሲሆን፣ ከዚያ ጊዜ አንስቶም የክለቡ የመጀመሪያ ተመራጭ የግብ ዘብ ሆኖ ቆይቷል።

ነገር ግን በቅርብ ጊዜያት በብቃቱ ላይ ትችቶች እየተሰነዘሩ የሚገኝ በመሆኑ አርሰናል በመጪው ክረምት የቼክን ቁጥር 1 ተሰላፊነት የሚፎካከር ግብ ጠባቂ እንደሚያስፈርም ይጠበቃል።

ዴቪድ ኦስፒና – 2019

ኮሎምቢያዊው ግብ ጠባቂ በመድፈኞቹ ያለው የኮንትራት ስምምነት ከ18 ወራት ያላነሰ ጊዜ ቢቀረውም በመጪው ክረምት ግን እንደሚሸጥ ይጠበቃል።

አርሰን ቬንገር ባለፈው ዓመት ግብ ጠባቂውን ለተጨማሪ የውድድር ዘመናት ለማቆየት ፈልገው የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂው ግን የቋሚ ተሰላፊነትን ለማግኘት ሲል ወደሌላ ክለብ የመሄድ ፍላጎት አለው።

ኤንስሌይ ማይትላንድ-ኒለስ – 2019

የአርሰናል የእግርኳስ ማሰልጠኛ ፍሬ የሆነው ተጫዋች በ2017/18 የውድድር ዘመን ሰብሮ በመውጣት አስደሳች ጊዜን በማሳለፍ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ማሳየት በቻለው ድንቅ ብቃት ምክኒያትም አርሰን ቬንገር ቀዳሚ የጨዋታ እቅዳቸው ላይ እንዲያካትቱ አስገድዷቸዋል።

ተጫዋቹ አዲስ ስምምነት ለመፈረም በመነጋገር ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ከክረምት በፊትም ፊርማውን እንደሚያኖር ይጠበቃል።

ካርል የንኪንሰን – 2020

ተከላካዩ የአምስት ዓመት የስምምነት ፊርማውን ለክለቡ ያኖረው በ2015 ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን በሻምፒዮንሺፑ ክለብ በርሚንግሃም በውሰት እያሳለፈ ይገኛል።

አርሰናል ባለፈው ዓመት ሊያዛውረው የነበረ ቢሆንም ተጫዋቹ ግን ወደክሪስታል ፓላስ ከመዛወር ይልቅ ቦታውን አስጠብቆ መቆየትን ምርጫው አድርጓል።

በመጪው ክረምት ግን ክለቡን እንደሚለቅ ይጠበቃል።

አሌክስ ኢዎቢ – 2020

ናይጄሪያዊው ተጫዋች በ2015/16 የውድድር ዘመን በዋናው ቡድን መታየት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ የአርሰን ቬንገር ተመራጭ ተጫዋች ለመሆን ጥረት ማድረጉን እንደቀጠለበት ይገኛል።

ከባለፈው ዓመት አንስቶ እያሳየ የሚገኘው ብስለት አዝጋሚ ቢሆንም አርሰን ቬንገር ግን በወደፊት ብቃቱ ላይ በተጫዋቹ ላይ ከፍተኛ ተስፋ አላቸው።

ሎረን ኮሽየልኒ – 2020

ፈረንሳያዊው ተከላካይ ወደክለቡ ከመጣበት 2010 አንስቶ ከፍተኛ ብቃቱን ሲያሳይ ቆይቷል።

ኮሺየልኒ በአሁኑ ጊዜ የክለቡ ምክትል አምበል ሲሆን ምንም እንኳ በተረከዙ ላይ የጉዳት ችግር ያለበት ቢሆንም በተከላካይ ክፍሉ ላይ ግን አሁንም ድረስ ወሳኝ ተጫዋች ነው።

መሐመድ ኤልኒኒ – 2020

አርሰናል በ2017 ለግብፃዊው ተጫዋች ከሌስተር ሲቲ የቀረበለትን የዝውውር ጥያቄ ተቀብሎ ነበር። ነገር ግን ተጫዋቹ በኤመራትስ ለመቆየት ወስኗል።

ተጫዋቹ በቡድን ስብስቡ ውስጥ ወሳኝ ሚኖ ያለው ተጫዋች መሆን የቻለ ሲሆን አዲስ የኮንትራት ስምምነት እንደሚቀርብለትም ይጠበቃል።

ሮብ ሆልዲንግ – 2020

ወጣቱ ተከላካይ ከቦልተን ክለቡን የተቀላቀለው በ2016 የነበረ ሲሆን ችልሲን በገጠሙበት የኤፍኤ ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ የመጀመሪያ ተሰላፊ መሆን ከቻለበት ጊዜ አንስቶ በቡድኑ ውስጥም የውድድር ዘመኑን በቋሚነት የመሰለፍ ዕድል በማግኘት አጠናቋል።

በወቅቱ ባሳየው ብቃት አድናቆት ቢቸረውም በሰሜን ለንደኑ ክለብ ሁለተኛ የውድድር ዘመኑ ያንን ጊዜ ለመድገም ተቸግሯል።

ሆልዲንግ በ2018/19 የውድድር ዘመን በውሰት እንዲያሳልፍ ወደሌላ ክለብ ሊዛወር ይችላል።

ሉካስ ፔሬዝ – 2020

ስፔናዊው አጥቂ ክለቡን በ2016 ቢቀላቀልም በአርሰን ቬንገሩ ቡድን የቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ፈፅሞ መግባት ሳይቻለው ቀርቷል።

በመጀመሪያ የውድድር ዘመን ቆይታው በፕሪሚየር ሊጉ ላይ በሚገባ ያልተሰለፈ ሲሆን፣ በ2017 ክረምት ወቅት ወደዲፖርቲቮ ላ ካሩኛ በውሰት እንዲጫወት ተልኳል።

ፔሬዝ ከስፔን ወደመድፈኞቹ ተመልሶ ለመጫወት ተቸግሮ የሚገኝ ቢሆንም ቦታውን ለማስከበር ዳግመኛ ወደአርሰናል የመመለስ ፍላጎት እንዳለው ግን ተናግሯል።

መሱት ኦዚል – 2021

ጀርመናዊው ተጫዋች የኮንትራት ማራዘሚያ ፊርማውን በውል ስምምነት ሰነዱ ላይ ያኖረው ከአንድ ዓመት በላይ ድርድር በማድረግ ጥር ወር ላይ ነበር።

ኦዚል ከሪያል ማድሪድ ለአርሰናል የፈርመው በ2013 ሲሆን፣ በኤመራትስም ትልቅ ስም ማፍራት ችሏል።

ተጫዋቹ በአዲስ የውል ስምምነቱ በአሁኑ ጊዜ 350,000 ፓውንድ ሳምንታዊ ደመወዝ በማግኘት የክለቡ ከፍተኛ ተከፋይ ነው።

ሄንሪክ ሚክሂታሪያን – 2021

ሚክሂታሪያን አሌክሲ ሳንቼዝን ወደማንችስተር ዩናይትድ እንዲዛወር ያደረገው የዝውውር ቅያሪ አካል በመሆን አርሰናልን የተቀላቀለው በጥር ወር ነበር።

ተጫዋቹ ከመሱት ኦዚል ጋር በጨዋታ አቀጣጠይነት ሚና በመጣመር በሰሜን ለንደኑ ክለብ ከወዲሁ ተፅእኖ ፈጣሪነቱን ማሳየት ጀምሯል።

ግራኒት ዣካ – 2021

አርሰናል ዣካን በ2016 ያስፈረመው ከጀርመኑ ክለብ ቦሩሲያ ሞንቼንግላድባኽ ነበር። ተጫዋቹ እስካሁን ሁለት የሚቃረኑ አስተያየቶች የሚሰነዘሩበት ተጫዋች እንደሆነ ይገኛል።

ነገር ግን በመጀመሪያ የውድድር ዘመኑ ቡድኑን በቀላሉ መቀላቀል ችሎ ከአራቱ ተከላካዮች ፊት በጥልቀት የተከላካይ አማካኝነት ሚናን በመወጣት በአርሰን ቬንገሩ ቡድን ውስጥ በሁሉም ጨዋታዎች ላይ የሚሰለፍ ተጫዋች እስከመሆን ደርሷል።

ካሊዩም ቻምበርስ – 2021

ወጣቱ እንግሊዛዊ ተከላካይ ባለፈው ክረምት ወደአርሰናል ዳግመኛ ከመመለሱ በፊት ያለፈውን የውድድር ዘመን በውሰት ያሳለፍው ለሚድልስብሮ በመጫወት ነበር።

ባለፈው ጥቅምት ወር አዲስ ኮንትራት ቀርቦለት በዚህ የውድድር ዘመን ለክለቡ የዩሮፓ ሊግ ጨዋታዎች ላይ እየተሰለፈ የሚገኝ ቁልፍ ተጫዋች መሆን ችሏል።

ይሁን እንጂ በሰሜን ለንደኑ ክለብ የሚኖረው ቆይታ ዘላቂ መሆን አለመሆኑም ገና ወደፊት የሚታይ ይሆናል።

ሽኮድራን ሙስታፊ – 2021

ጀርመናዊው ተጫዋች በ2016 አርሰናልን ከተቀላቀለ በኋላ በክለቡ የነበረው ጅማሮ አስቸጋሪ የሚባል ነበር። ባለፈው ክረምትም የሚሸጥ ተጫዋች ሊሆን እንደሚችል የሚገልፁ አስተያየቶች ሲሰጡበት ነበር።

ተጫዋቹን ለማስፈረምም የኢንተር ሚላን ስም በከፍተኛ ሁኔታ ተያይዞ የነበረ ቢሆንም ሙስታፊ ግን ከሎረን ኮሸልኒ ጋር በመጣመር በአርሰን ቬንገር የመሃል ተከላካይ ስፍራ ላይ እየተጫወተ መቆየትን መርጧል።

ፒየር ኤሜሪክ-አውባምያንግ – 2022

አርሰናል አውባምያንግን ከዶርትሙንድ በማስፈረም በተመሳሳዩ ደግሞ ኦሊቪየ ዥሩን ለቼልሲ የሸጠው ባለፈው ጥር ወር የዝውውር መስኮት ወቅት ነበር።

አርሰናል አሌክሲ ሳንቼዝን ወደማንችስተር ዩናይትድ እንዲዛወር በማድረጉ ያጣውን ግብ አስቆጣሪነት ሚና ጋቦናዊው ተጫዋች እንደሚወጣው ተስፋ በመድረግም ነበር ያዛወረው።

አሌክሳንደር ላካዜቴ – 2022

ፈረንሳያዊው አጥቂ በ2017 ከፈረንሳዩ ክለብ ሊዮን አርሰናልን የተቀላቀለ ሲሆን፣ ኦውባምያንግ ከመፈረሙ በፊትም ዝውውሩ የአርሰናል የዝውውር ክበረወሰን በመሆን ቆይቶ ነበር።

ላካዜቴ በሰሜን ለንደን ጥሩ ጅማሮ የነበረው ቢሆንም፣ የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ከገባ በኋላ በጉልበቱ ላይ የቀዶ ጥገና ከማድረጉ በፊት የብቃት መውረድ ችግር ውስጥ ገብቷል።

ሲያድ ኮላሲናች – 2022

ቦስኒያዊው ተከላካይ ላካዜቴ ክለቡን ከመቀላቀሉ አንድ ወር በፊት ነበር ከጀርመኑ ክለብ ሻልከ በነፃ ዝውውር ለአርሰናል የፈረመው።

ኮላሲናች የውድድር ዘመኑ እየገፋ ሲመጣ የመጫወቻ ቦታውን እያጣ በመምጣት በአሁኑ ጊዜ በተቀያሪ ተጫዋችነት አያገለገለ ይገኛል።

ሄክቶር ቤለሪን – 2023

ስፔናዊው ተጫዋች የዓለማችን ምርጡ ወጣት የመስመር ተከላካይ በመሆን ረጅም ጊዜ የሚያቆየውን የስድስት ዓመት ከግማሽ የኮንትራት ስምምነት የፈረመው በ2016 ነበር።

ሆኖም ክለቡን እንደሚለቅ እየተነገረ በቆየባቸው ባለፉት 12 ወራት ግን በክለቡ ያለው ለውጡ እየደበዘዘ መጥቷል።

ባርሴሎና፣ ማንችስተር ሲቲ፣ ጁቬንቱስና ማንችስተር ዩናይትድ ከተጫዋቹ የዝውውር ጉዳይ ጋር ስማቸው በከፍተኛ ሁኔታ የተያያዙ ክለቦች ናቸው።

ኮንስታንቲኖስ ማቭሮፓኖስ – 2023

አርሰናል ወጣቱን ግሪካዊ ተከላካይ ከካፓስ ጂያኒናን ክለብ ያስፈረመው በጥር ወር ነበር። ተጨዋቹ አዲሱ የክለቡ የተጫዋቾች መልማይ በሆኑት ስቨን ሚስሊንታት ጥቆማ መሰረት የፈረመ የመጀመሪያው ተጫዋችም ነው።

Advertisements