ሴስክ ፋብሪጋዝ ወደ አርሴናል መመለስ እንደሚፈልግ አሳወቀ

ለቼልሲ እየተጫወተ የሚገኘው የቀድሞ የአርሰናል ተጫዋች የነበረው ሴስክ ፋብሪጋዝ አንድ ቀን የመድፈኞቹ አሰልጣኝ ሆኖ ወደ ለንደን መመለስ እንደሚፈልግ ተናግሯል።

2003 ላይ ወደ አርሰናል በ 16 አመቱ መቀላቀል ከቻለ በኋላ በወጣትነቱ ከመድፈኞቹ ጋር ተፅእኖ መፍጠር ችሏል።

2011 ላይ ወደ ልጅነት ክለቡ ወደ ሆነው ባርሴሎና ዝውውሩን ገፍቶ እንዲጠናቀቅ በማድረግ ከአርሰናል ጋር መለያየት ችሎ እንደነበር ይታወሳል።

ተጫዋቹ ከጥቂት አመታት የባርሴሎና ቆይታው በኋላ 2014 ላይ ወደ መድፈኞቹ ለመመለስ ያቀረበው ጥያቄ በአርሰን ዌንገር ተቀባይነት ባለማግኘቱ ወደ ቼልሲ አቅንቷል።

ፋብሪጋዝ ከቼልሲ ጋር ወደ ኤምሬትስ ሲያቀና በደጋፊዎች የተደባለቀ ስሜት እየቀረበለት ቢገኝም ወደፊት ግን ወደ መድፈኞቹ በአሰልጣኝነት ለማቅናት ፍላጎት እንዳለው አሳውቋል።

በትዊተር ከደጋፊዎች ጋር ቃለ መጠይቅ የነበረው ፋብሪጋዝ ወደ አርሰናል መመለስ እንደሚፈልግ ተጠይቆ “አዎ አንድ ቀን በአሰልጣኝነት መመለስ እፈልጋለው።” ሲል ምላሹን ሰጥቷል።

ፋብሪጋዝ አያይዞ 2011 ላይ በሰሜን ለንደን ደርቢ ስፐርስ ላይ ያስቆጠራት ጎል በአርሰናል ቆይታዉ ቅድሚያ የሚሰጣት ጎል መሆኑን አሳውቋል።

ስፔናዊው አማካይ ከመድፈኞቹ ጋር በስምንት አመት ቆይታው ከ 300 በላይ ጨዋታዎች ላይ መሳተፍ ችሏል።

Advertisements