ለውጥ / የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ያስተላለፋቸው አዳዲስ ደንቦች አንደምታ

የአውሮፓን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው የአውሮፓ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (UEFA) በሚያሰናዳቸው ዋነኛ የክለብ ውድድሮች(ሻምፒዮንስ ሊግ ፣ ዩሮፓ ሊግና ሱፐር ካፕ) ላይ የተወሰኑ የህገ ደንብ ማሻሻያዎችን ያፀደቀ ሲሆን ደንቦቹንም “በተለይ የአሰልጣኞችን አማራጭ ማስፋት የሚችሉ ” ሲል ገልጿቸዋል፡፡
አንድ ተጫዋችን በአንድ የውድድር ዘመን ለሁለት የተለያዩ ክለቦች መጫወትን የሚፈቅደው ህግ

ለአመታት እንደምናውቀው የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በሚያደርጋቸው የሻምፒዮንስ ሊግና የዩሮፓ ሊግ ውድድሮች ላይ አንድ ተጫዋች በአንድ የውድድር አመት በተመሳሳይ ውድድር ለሁለት ክለቦች መጫወትን የሚከለክል ህግ ሲሰራበት ቆይቷል ፤ ለዚህ ደንብ የቅርቡ ምሳሌ የባርሴሎናው አማካይ ፍሊፕ ኮቲንሆ ነው፡፡

ብራዚላዊው በጥሩ የዝውውር መስኮት ሊቨርፑልን ለቆ ለባርሰሎና የፈረመ ቢሆንም በውድድር አመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ በሻምፒዮንስ ሊጉ የሊቨርፑልን መለያ ለብሶ የተጫወተ በመሆኑ በሁለተኛው የአመቱ አጋማሽ በዚሁ ውድድር ለባርሴሎና መጫወት አይችልም ፤ በመሆኑም ተጫዋቹ ክለቡን በዚህ የውድድር አመት ማገልገል የሚችለው በአገር ውስጥ ውድድሮች ብቻ ነው፡፡ 

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበሩ አዲስ ውሳኔ ከቀጣዩ አመት ጀምሮ ክለቦች በጥር የዝውውር መስኮት የሚገዟቸው ተጫዋቾች በመጀመሪያ ክለባቸው ተሳታፊ የነበሩ ቢሆንም ለውድድሩ ማስመዝገብ እንዲችሉ የሚፈቅድ ነው፡፡
አራተኛ ተቀያሪ ተጫዋች በጥሎ ማለፍ ጭማሪ ሰዓት መጠቀም

እንደተለመደው በአንድ የውድድር ጨዋታ ላይ ከፍተኛው ተቀይሮ የሚገባ ተጫዋች መጠን ሶስት ነው ፤ ይህ ነባር ደንብ ግን በአዲሱ የእግር ኳስ ማህበር ደንብ መሰረት ወደአራት ተጫዋቾች ከፍ የሚልበት አሰራር የተዘጋጀ ሲሆን ህጉ ግን ተግባራዊ የሚሆነው በጥሎ ማለፍ ጨዋታ የ 30 ደቂቃ ጭማሪ በሚኖርበት ወቅት ብቻ ይሆናል ፤ በተጨማሪም የፍፃሜ ጨዋታዎች ላይ(ሻምፒዮንስ ሊግ ፣ ዩሮፓ ሊግ እና ሱፐር ካፕ) ክለቦች 23 ተጫዋቾችን(12 የተቀያሪ አማራጮችን)አስመዝግበው የሚጫወቱበት አሰራር ከቀጣዩ አመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው ደንብ አካል ሆኗል፡፡ በእስካሁኑ አሰራር ክለቦች በፍፃሜም ሆነ በሌሎች የጨዋታ ደረጃዎች 18(ሰባት የተቀያሪ አማራጮች) ተጫዋቾችን አስመዝግበው ወደሜዳ እንደሚገቡ ይታወቃል፡፡

የምድብ ጨዋታዎች ሰዓት ለውጥ

የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች በተለምዶ 3:45 እና 4:45 ይደረጉ የነበረ ሲሆን ይህ የጨዋታ ሰዓት በአዲሱ ደንብ መሰረት በ 4:00 እና 5:00 የሚካሄድ ይሆናል (4:00 እና 5:00 እንደወቅቱ የሚቀያየር መሆኑን ልብ ይሏል) በተጨማሪም ማክሰኞና ረቡዕ ከሚደረጉ የምድብ ጨዋታዎች ሁለቱ(ማክሰኞ ሁለት ረቡዕ ሁለት) የጨዋታ ሰዓታቸው ወደፊት ተጠግቶ 1:55 ወይም 2:55 (1:55 እና 2:55 የሚካሄዱ ጨዋታዎች እንደወቅቶቹ የሚለያዩ መሆኑን ልብ ይሏል) የሚካሄዱ ይሆናል፡፡

ማህበሩ ያፀደቃቸው አዳዲስ ደንቦች ከቀጣዩ አመት ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆኑ ማህበሩ አረጋግጧል፡፡

Advertisements