ያላቸውን ድንቅ ብቃት አውጥተው ማስመስከር ሳይችሉ የቀሩ 11 ተስፈኛ ተጫዋቾች

ነገ (ረቡዕ) የ2018 የቀጣዩ ዘመን (Next Generation) ምርጥ ተስፈኛ የሚሆነው ተጫዋች ይፋ ይሆናል። ኢትዮ አዲስ ስፖርትም ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ድንቅ የሆነ ተስጥኦ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች በዓለም አደባባይ ላይ አውጥተው በማሳየት ዘላቂ ብቃት ማሳየት ሳይችሉ ቀርተው የተጣለባቸው ተስፋ እንደጉም በኖ የጠፋባቸውን 11 ተጫዋቾችን ልታስተውስዎ ወደደች።

* ፅሁፉን አንብበው ሲጨርሱ ሃሳብና አስተያየትዎን ይሰጡን ዘንድም ጋብዘናል።

1. አድሪያኖ

አድሪያኖ እ.ኤ.አ. በወርሃ የካቲት 2000 የፍላሚንጎን የመጀመሪያ ቡድን መቀላቀል የቻለው ገና በ17 ዓመት ለጋ ዕድሜው ነበር። አድሪያኖ በመጀመሪያው የፕሮፌሽናል እግርኳስ ህይወቱ ላይ ድንቅ ብቃቱን ማሳየት ችሎ ከአንድ ዓመት በኋላ ኢንተር ሚላን 7 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ እንዲያደርግበት ማስገደድ ችሏል። በፊዮረንቲና እና ፓርማ የነበረው አሰደናቂ የውሰት ቆይታ ጊዜ በክለቡም ሆነ በሃገሩ የሮናልዶ ሁነኛ ተተኪ እንደሚሆን ተተንብዮለት ስሙ በከፍተኛ ሁኔታ ጣራ እንዲነካም ሆኗል። ይሁን እንጂ ብራዚል በ2004 የኮፓ አሜሪካ እና 2005 የኮንፌዴሬሽን ዋንጫዎችን እንድታነሳ ቁልፍ ሚና የነበረው ተጫዋች የንግስና ዘውዱን ለመድፋት በ2004 የአባቶን ህልፈት ተከትሎ የገጠመው ጭንቀት እና የአልኮል ሱስ መሰናክል ሆኖበታል።

2. ፍሬዲ አዱ

ገና በ14 ዓመት አፍላ ዕድሜው “አዲሱ ፔሌ” የሚል ስያሜን ቢያገኝም እስከ28 ዓመት ዕድሜው ግን ከአንዱ ክለብ ወደሌለው ክለብ ሲንከራተት ቆይቷል። እንደአዱ የነበረው ከፍተኛ ክብር ቁልቁል የወረደ ዝና ያለው ተጫዋች ማግኘትም ይቸግራል። አዱ በ16 ዓመቱ ለብሄራዊ ቡድኑ መጫወት የቻለ ሲሆን፣ ከአንድ ዓመት በኋላ አጥቂው ወደቤኔፊካ አምርቷል። ይሁን እንጂ ተጫዋቹ በቤኔፊካው ኢስታዲዮ ዳ ሉዝ ብቃቱን ማስመስከር ሳይችል ቀርቷል። ከዚያ በኋላም ለመጨረሻ ጊዜ በ2017 ታምፓ ቤይ ሮውዲስ የተባለ ክለብ ከመድረሱ በፊት ሰርቢያ እና ፊንላንድን ጨምሮ በርካታ ክለቦች ውስጥ እየተዘወወረ በመጫወት ብቃቱን ማሳየት ያልቻለና መረጋጋት ያጣ ተንከራታች ተጫዋች ለመሆን በቅቷል።

3. አንደርሰን

አንደርሰን ስቴቨን ጄራርድ ማግኘት ያልቻለውን አራት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ማንሳት መቻሉን በማስታወስ ያገኛቸው የክብር ሜዳዮች ምርጥ ተጫዋች እንደሚያሰኙት ያምናል። ይሁን እንጂ ብራዚላዊው የቀድሞ የፓርቶ ተጫዋች የቀድሞው የሊቨርፑል አምበል “በእግርኳስ ታሪክ ላይ” ያላገኘውን ማግኘት ቢችልም፣ ከባከነ ክህሎቱ ውጪ ሌላ በእግርኳሱ ዓለም የሚታወስ ነገር የለውም። በእርግጥ ተጫዋቹ በታሪካዊው የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን “የተለየ ነገር” ያለው ተጫዋች እንደነበር ተሞካሽቶ ቢገለፅም ነገር ግን በነበረበት የፕሮፌሽናልነት ችግር ምክኒያት ገና በ26 ዓመት ዕድሜው በ2015 ክለቡን ለቋል። በአሁኑ ጊዜ ወደብራዚል ተመልሶ ከኮሪቲባ ክለብ ለኢንተርናሲዮናል ክለብ በውሰት ተሰጥቶ በመጫወት ላይ ይገኛል።

4. አንቶኒዮ ካሳኖ

“ጥሩ የእግርኳስ ህይወት የነበረኝ ላለመሆኑ የራሴው ጥፋት ነው።” ሲል አንቶኒዮ ካዛኖ በ2013 ስኬታማ አንዳልነበረ አምኖ “ካለኝ ነገር 50 በመቶ ያህሉን እንኳ ላስካ አልቻልኩም።” ሲልም ገልፅዋል። ካዛኖ አልተሳሳተም። ተጫዋቹ ተፈጥሯዊ ብቃት ያለው ተጫዋች እንደሆነ የታወቀው ገና በ17 ዕድሜው የትውልድ ከተማ ክለቡ ባሪ ኢንተርን እንዲያሸንፍ ያደረገች ዝነኛ ግብ በማስቆጠር ነበር። ይሁን እንጂ እንደሮማ እና ሪያል ማድሪድ ባሉ ክለቦች ውስጥ ተጫውቶ ቢያሳልፍም፣ ጣሊያናዊው አጥቂ ግን ሙሉ አቅሞን አውጥቶ ስለመጫወቱ ፈፅሞ አይታወስለትም። ይልቁንስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሊበቃባቸው በሚገባው ዓመታት አብዝቶ መመገብን እና ሴት አውል መሆንን መርጧል። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ካለፈው ሃምሌ ወር አንስቶ ክለብ አልባ ተጫዋች ሆኖ ይገኛል።

5. ዴኒልሰን

ዴኔልሰን የዓለም ዋንጫ አሸናፊ እና በአንድ ወቅት የዓለማችን ውድ ተጫዋች ነበር። ይሁን እንጂ የዴነልሰን የእግርኳስ ህይወት ጫፍ ከመድረስ ይልቅ ቁልቁለታማ ጉዞው ያመዝናል። በእርግጥ በ1998 የዓለም የዝውውር ክበረወሰን በሆነ 21.5 ሚ.ፓውንድ ሪያል ቤቲስን ከመቀላቀሉ በፊት በሳኦ ፓሎ ቡድን ውስጥ በ17 ዓመት ዕድሜው ሰብሮ መውጣታ ከቻለው ከምትሃተኛው የግራ እግሮቹ ብዙ ነገሮች የሚጠበቁበት ተጫዋች ነበር። ይሁን እንጂ ብራዚለዊው ተጫዋች ይበልጥ እየጎመራና እየተሻሻል ከመምጣት ይልቅ እየደበዘዘ የመጣው በቶሎ ነበር። ተጫዋቹ ሁሉንም ባስማማ መልኩ እግርኳስ ከማቆሙ በፊት በ1998 የዓለም ዋንጫ የብራዚል ብሄራዊ ቡድን ለአንድ አየር መንገድ በሰራው ተወዳጅ ማስታወቂያ ላይ ትልቅ ሚና ነበረው። በሳኡዲ አረቢያ፣ በአሜሪካ፣ ቪየትናም እና ግሪክ ሃገራት እየተዘዋወርም ተጫውቷል።

6. ዲያጎ

ዚኮ በአንድ ወቅት እሱና ዲየጎ የሚጋሩት ተመሳሳይ የማጥቃት ሚና እንዳለቸው ገልፃ ነበር። “እሱ በነበረው የጨዋታ ሚና እና የቅጣት ምት የሚመታበት መንገድ በጣም ተመሳሳይነት እንዳለን እውነት ነው።” ሲል ብራዚላዊው ዝነኛ ስለሃገሩ ልጅ ተናግሯል። ይሁን እንጂ ዚኮ የሴሎሳዎቹን 10 ቁጥር በመልበሱ የምንጊዜውም ምርጥ ተጫዋችነቱ ቢታወስም ነገር ግን ይህ ክብር በዲያጎ ሊደገም አልቻለም። ዲያጎ ጥንካራ ተጫዋች የነበረ ሊሆን ይችላል። በ16 ዓመቱም በሳንቶስ ሰብሮ መጣት የቻለ ወጣት ተስፈኛም ነበር። ነገር ግን ይህ ድንቅ ብቃቱ በፓርቶ እና ጁቬንቱስ ወረደ። በእርግጥ በወርደን ብሬመን እና አትሌቲኮ ማድሪድ በድንገት ብቃቱ መፈንጠቅ ችሎ የነበረ ቢሆንም መልካም ስነምግባር ግን አብሮት አልነበረም።

7. ቦዣን ኪርኪች

ቦዣን በ2007-08 የውድድር ዘመን 10 ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ ባሳየው ታላቅ አጨዋወት በእግርኳስ ታሪክ ላይ በላ ሊጋ የጨዋታ መርሃ ግብሮች ባርሴሎናን በመወከል የሊዮኔል መሲን ቦታ እንደሚረከብ ተስፋ የተጣለብት ወጣት ተጫዋች ነበር። ያን ጊዜም የአላቬሱ አጥቂ ገና 17 ዓመቱ ነበር። ይሁን እንጂ የፊት ተጫዋችነት ታላቅ ሚናውን ከባርሴሎና አንስቶ፣ በኤሲ ሚላን፣ አያክስ ስቶክን ጨምሮ ማስመከር ቸግሮት ታይቷል። በእርግጥ በአንድ ወቅት በፍራንክ ራይካርድ እንደ”ከበረ” ተጫዋች ቢቆጠርም በካታላኑ ክለብ በአንድ የውድድር ዘመን የሳየውን ብቃት ግን ዳግመኛ ማሳየት ሳይችል ቀርቷል።

8. ፌዴሪኮ ማቼዳ

በ2008-09 የውድድር ዘመን በመጨረሻ ሰዓት በአስቶንቪላ ላይ ባስቆጠረው የአሸናፊነት ግብ ማንችስተር ዩናይትድ ወደዋንጫ ተፎካካሪነቱ እንዲመለስ በማድረግ በኦልትራፎርድ በቶሎ በደጋፊዎች ልብ ውስጥ ተወዳጅነትን ለማግኘት ከማርኮስ ራሽፎርድ ቀጥሎ እንደፌዴሪኮ ማቼዳ የቀደመ ወጣት ተጫዋች ማግኘት ይቸግራል። “ማርከስ ጠንክሮ መስራት መቀጠል ይኖርበታል። ራስህን አግዝፈህ መሻሻል የለብህም። በጉዳትም ዕድለኛ መሆን አለብህ።” ሲል ጣሊያናዊው ተጫዋች በ2016 ተናግሯል። አሌክስ ፈርጉሰን ማቼዳ “ድንቅ የሆነ ክህሎት” አለው ብለው ባየስቡም ነገር ግን “ምርጥ አስቸጋሪ” ተጫዋች መሆኑንም ገልፀዋል። ያለመታደል ሆኖ ግን ማቼዳ ከፍተኛ ደረጃ የሚያደረሰው ነገር አልነበረውም። የ26 ዓመቱ ተጫዋች የክለብ ስኬቱ ማሽቆልቆሉን ተከትሎ በአሁኑ ጊዜ በሴሪ ቢው ክለብ ኖቫራ እየተጫወተ ይገኛል።

9. አሌክሳንድሮ ፓቶ

አሌክሳንደር ፓቶ ገና በ19 ዓመት ዕድሜው በኤሲ ሚላን የመጀመሪያ ተመራጭ አጥቂ መሆን እንዲሁም በብራዚል ብሄራዊ ቡድን ውስጥ ሶስት ጨዋታዎች መጫወት ችሏል። “ዳክዬው” አሁን በ28 ዓመት ዕድሜው በታንዢን ኩዋንዢን ክለብ አዎንታዊ ብቃት ለማሳየት እየታገለ እና ከምንጊዜውም በላይ ከብሄራዊ ቡድን ተሳትፎው ርቆ በቻይና ይገኛል። ያለጥርጥር ፓቶ በአንድ ወቅት ተከላካዮችን የሚያርድበት ፍጥነቱን ጉዳት ነጥቆታል። ነገር ግን አዕምሯዊ ጥንካሬው በተለይም በኮሮንቲያስ ክለብ ባሳየው መጥፎ የሚባል ጊዜ በተዳጋጋሚ ጥያቄ ሲያስነሳብትም ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜ በእሱ ላይ ያለው እውነተኛ ፍራቻም አጥቂው የነበሩት ድንቅ ጊዜያት በእጅጉ እየራቁ እና እየተዘነጉ መምጣታቸው ነው።

10. ጀርሜን ፔናንት

ጀርሜን ፔናንት በ1999 አርሰናል በ15 ዓመት ዕድሜው ከኖትስ ካውንቲ በ2 ሚሊዮን ፓውንድ ሲያስፈርመው በታዳጊዎች ማሰልጠኛ ውስጥ ሆኖ የፈረመ የብሪቴን ውዱ ተጫዋች ነበር። ነገር ግን አርሰን ቬንገር በተጫዋቹ መጥፎ የሚባል የጊዜ አጥባበቅ እና የበዛ መሸታ ቤት የማዘውተር ህይወት ትዕግስታቸው እንዲሟጠጥ ሆኗል። በእርግጥ በኋላ ላይ ለታደጊዎች ምን አይነት ምክር እንደሚለግስ ሲጠየቅ ፔናንት “ከሴቶች ራቁ!” ሲል ቀልዷል። ይሁን እንጂ ራሱ የአልኮል መጠጥ ችግር የነበረበት ሲሆን፣ በርሚንግሃም በነበረበት ወቅትም ጠጥቶ በማሽከርከር ጥፋት ለሶስት ወራት ለእስር ተዳርጎ ነበር። ፔናንት በ2007 የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ለሊቨርፑል ድንቅ ብቃታቸውን ማሳየት ከቻሉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ በመሆን የተጫዋችነት ህይወቱ ላይ ጉልህ ነገር ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን የነበረበት የስነምግባር ችግር ዋጋ አስከፍሎታል። እናም በአሁኑ ጊዜ ከቢለሪሲ ታውን ክለብ ጋር ከተለያየ በኋላ ክለብ አልባ ሆኖ ይገኛል።

11. ኻቪየር ሳቪዮላ

ሳቪዮላ በ1999 ባርሴሎናን ሲቀላቀል ዓለም በእግሩ ላይ ነበረች። በሪቨር ፕሌት ሁለት ዋንጫዎችን በማንሳት እና የደቡብ አሜሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች በመሰኘት ገና በ19 ዓመቱ ልዕለ ተጫዋችነት ክብርን ማግኘት ችሎ ነበር። የኑ ካምፕ የተጫዋችነት ጅማሮውም ብሩህ ነበር። ነገር ግን ብቃቱ ጫፍ ደርሶ በጎመራበት አመት ፍራንክ ራይካርድ በአሰልጣኝነት ወደባርሴሎና መምጣቱ በካታሎኑ ክለብ ያለው ህይወቱ ስለማብቃቱ ምልክት ሆነ። ሳቪዮላ ዳግመኛ ወደሪቨር ፕሌት ተመልሶ የአርጄንቲናውን የኮፓ ሊበርታዶስ ሜዳይ ማጥለቅ ችሏል። ነገር ግን ከዚያ በኋላ የቀድሞውን ብቃት መድገም አልቻለም። “ያለፈውን ጊዜ ስመለከት ይበልጥ መጫወት ብችል ኖሮ ስል እመኛለሁ።” ሲል በለላ ሊጋው ላይ ስለነበረው ጊዜ ተናግሮ ነበር።

Advertisements