“አርጀንቲናዊያን ሜሲን በቡድናቸው መያዛቸው ፈጣሪን ማመስገን ይገባቸዋል”- ዲያጎ ኮስታ

ትናንት ምሽት በማድሪድ ዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ስታድየም በአቋም መፈተሻ ጨዋታ ስፔን አርጀንቲናን 6-1 ካሸነፈች በኋላ ዲያጎ ኮስታ ሊዮ ሜሲን ለሚተቹ አርጀንቲናዊያን “እሱ ቡድናችሁ ውስጥ ስላለ ፈጣሪን ልታመሰግኑ ይገባል” ሲል ድጋፉን ሰጥቷል።

ሊጀመር ጥቂት ወራት ብቻ በቀረው የ2018 የአለም ዋንጫ ዝግጅት ሀገራት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎች እያደረጉ ይገኛሉ።

ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ እየተደረጉ ባሉት ጨዋታዎች በአለም ዋንጫው ላይ የሚጠበቁ ቡድኖች የተሳተፉበት ተጠባቂ ጨዋታዎች ተደርገዋል።

ከተጠባቂዎቹ ውስጥ ትናንት ምሽት ስፔን ከላቲኗ አርጀንቲና ጋር ያደረጉት ጨዋታዎች አንዱ ሲሆን በጨዋታው ስፔን 6-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፋለች።

ሊዮ ሜሲን ሳትይዝ ወደ ሜዳ የገባችው አርጀንቲና ያለ የአምስት ጊዜ የባሎንዶር አሸናፊው ምን ልትመስል እንደምትችል ያሳየችበት ምሽት ነበር።

ከጨዋታው በኋላ የስፔኑ አጥቂ ዲያጎ ኮስታ ይህንኑ የሚያጠነክር አስተያየት ሰጥቷል።

ጎል በማስቆጠር ተሳታፊ የነበረው ኮስታ ከጨዋታው በኋላ “የአርጀንቲና ህዝብ ሜሲን በጣም ይተቸዋል ነገርግን እሱ ሳይኖር ቡድኑ ምን እንደሚመስል ተመልክተዋል።ያለ እሱ ቡድኑ የተለየ ነው።የሜሲን አይነት ተጫዋች ልትተቸው አይገባም፣የሱ አይነት ተጫዋች ስላላቸው ፈጣሪን ማመስገን ይኖርባቸዋል።” ሲል ተናግሯል።

አርጀንቲና በአምስት ጎል ልዩነት ለመጨረሻ ጊዜ የተሸነፈችው በ 2010 የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ላይ በቦሊቪያ ሲሆን 1958 ላይም በተመሳሳይ በቺኮስላቫኪያ 6-1 ተሸንፋ ነበር።

የወቅቱ የቡድኑ አምበል የሆነው ሊዮ ሜሲ አርጀንቲና ለ 2018 የአለም ዋንጫ ለማለፍ አጣብቂኝ ውስጥ በገባችበት የመጨረሻ ጨዋታ ሀትሪክ በመስራት ቡድኑን ተሸክሞ ወደ ራሺያው የአለም ዋንጫ እንዲገባ ማድረጉ ይታወሳል።

🗣️

Advertisements