ሎው በብራዚል የደረሰባቸው ሽንፈት አላሳሰባቸውም

የጀርመን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ዦአኪም ሎው የዓለም ሻምፒዮናዋ ሃገር በበርሊን ባደረገችው ጨዋታ በብራዚል 1ለ0 ተሸንፋ ከዚህ ቀደም የነበራት በ22 ጨዋታዎች ላይ ያለመሸነፍ ጉዞ መገታቱ አላስጨነቃቸውም።

ጀርመን በ2014 የዓለም ዋንጫ ሴሌሳዎቹን 7ለ1 በሆነ ሰፊ ውጤት ካሸነፈች ወዲህ ባደረገቱ የመጀመሪያ ጨዋታቸው በ37ኛ ደቂቃ ላይ በጋብሬል ኼሱስ በጭንቅላት ተገጭታ የተቆጠረችው ግብ የእንግዳዋን ቡድን ልዩነት በጉልህ ከማሳየቷም በላይ ዳይ ማንሻፍቶቹ በ2016 የአውሮፓ ዋንጫ በፈረንሳይ 2ለ0 ከተረቱ በኋላ የደረሰባቸው የመጀመሪያው ሽንፈት ሆኗል።

የጀርመን በ22 ጨዋታዎች ላይ ያለመሸነፍ ጉዞ በብራዚል የ1ለ0 ድል ሊገታ ችሏል

ከአራት ዓመታት በፊት ቡድናቸውን ለታላቁ የእግርኳስ ክብር ማብቃት የቻሉት ሎው ሻምፒዮንነታችውን በመጪው የሩሲያ ዓለም ዋንጫ ዳግመኛ ለማስከበር በሚያደርጉት የዝግጅት ጨዋታ ላይ በደረሰባቸው ሽንፈት ቡድናቸው እንደማያሳስባቸው ተናግረዋል።

“የቱንም ያህል በጥሩ ሁኔታ ቢዘጋጅም ሁሉም ቡድን መጥፎ ቀን ሊገጥመው ይችላል።” ሲሉ ሎው ተናግረው “ቡድናችን እንዴት መጫወት እንዳለበት እና ምን አይነት አዕምሯዊ ዝግጅት እንዳለን አውቃለሁ። በእርግጥም በጣም አብዝቼ አልጨነቅም።

“ስለዚህ በብራዚል 1ለ0 መሸነፋችን አያስጨንቀኝም።” ብለዋል።

ሎው አክለውም በቲቴ የተመራው ተጋጣሚያቸው በሜዳው የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል መጫወቱን መረዳታቸውንም ገልፀዋል።

“የብራዚላዊያን መንፈስ ሰላም የሚያገኝ ከሆነ ያ ፍፁም ጥሩ ነገር ይሆናል።” በማለት ጀርመናዊው አሰልጠኝ ተናግረዋል።

“ብራዚላውያኑ በከፍተኛ መነሳሳት፣ በከፍተኛ ጥረት እና በከፍተኛ ትኩረት ወደጨዋታው እንደሚገቡ የሚጠበቅ ነው። ከዚያ የ7ለ1 ውጤት በኋላም ይህ እንደሚሆን ልትጠብቅ ትችላለህ።

“ያን ሽንፈትም በዛሬው ድል ለማጥፋት ተስፋ አድርገው ሊሆን ይችላል።” ሲሉ የብራዚላውያኑ ድል የጀርመን ደግሞ ሽንፈት እንዳላስገረማቸው ገልፀዋል።

Advertisements