ገድል / በጦርነት የደቀቀችው የመን በአሰልጣኝ አብረሀም መብርሀቱ እየተመራች በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በእስያ ዋንጫ መሳተፍ የሚያስችላትን ትኬት ቆረጠች

በቀውስ ውስጥ ሆና ያለፉትን አራት አመታት ያሳለፈችው የመን ለመጀመሪያ ጊዜ ለእስያ ዋንጫ በማለፍ አዲስ ታሪክ ስትሰራ ሰሜን ኮሪያና ፊሊፒንስም የውድድሩን ትኬታቸውን ቆርጠዋል።

ያለፉትን አራት አመታት በጦርነት እየታመሰች የምትገኘው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገሯ የመን በኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ አብረሀም መብርሀቱ እየተመራች በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ለእስያ ዋንጫ መብቃት ችላለች።

በሀገሪቱ ባለው የእርስበርስ ጦርነት ምክንያት ጨዋታዋን በኳታር ለማድረግ የተገደደችው የመን በሌላኛው የምድብ ጨዋታ ታጃኪስታን በፊሊፒንስ 2-1 በመረታቷ የምሽቱን ጨዋታዋን የጀመረችው ለዋንጫው ማለፏን ቀድማ በማረጋገጥ ነበር። 

ፊሊፒንስን ተከትላ ወደ እስያ ዋንጫ ማለፏን ቀድማ ያረጋገጠችው የመን በምሽቱ የዶሀ ጨዋታ ላይም ኔፓልን አስተናግዳ 2-1 ስታሸነፍ ወደ እስያ ዋንጫ ያለፈችበትን ክስተት ይበልጥ ያሳመረውን ድል በአብዱልዋሲ አል ማታሪ የ 24 እና 84 ደቂቃዎች ግቦች አግኝታለች፡፡ 

ያለፉትን አራት አመታት ከላይ የሳውዲን የአየር ጥቃት ከስር የእርስበርስ ውጊያ ሲለበልባት የከረመችው የመን ከ 2014 አንስቶ የእግር ኳስ ሊጓ ተቋርጦ እግር ኳሷ ችግር ውስጥ ቢገባም ሁኔታውን ያስረሳና የሀገሪቱን ዜጎች የተሟጠጠ ተስፋ በመጠኑ የሚመልስ ውጤትን አስመዝግባ የህዝቦቿን አንገት ቀና ማድረግ ችላለች።

ከጦርነቱ ሰቆቃ ጋር በተያያዘ እንደአብዛኛው የሀገሪቱ ዜጎች የየመን የተወሰኑ ተጫዋቾች ሀገራቸውን ለቀው ህይወታቸውን ማቆየት እና እግር ኳስን በመደበኛ መልኩ የመጫወት እድል ሊያገኙበት ወደሚችሉበት ሀገራት እግሬ አውጪኝ ብለው መሰደዳቸው ይታወቃል። 

በዚህ ሁሉ መሀከል ግን ከሁለት አመት በፊት በዚህ በመጋቢት ወር የሀገሪቱን ብሔራዊ ቡድን ለማሰልጠን ከባዱን ሀላፊነት የተረከበው ኢንስትራክተር አብርሀም ከየመን ጋር ያለውን የቆየ ቁርኝት ይበልጥ ያደመቀ ገድልን በጦርነት ለደቀቀችው ሀገር እና ህዝቦቿ ማበርከት ችሏል።

በ 2013 የየመንን ኦሎምፒክ ስብስብ እየመራ ወደ እስያ ዋንጫ ከ 22 አመት በታች ፍልሚያ አምርቶ የነበረው አብርሀም በሀገሪቱ የእግር ኳስ ማህበር ውስጥ የቴክኒካል ክፍል ሀላፊ ሆኖ መስራት ድረስ መጓዙ የመካከለኛው ምስራቋን ሀገር እግር ኳስ በሚገባ እንዲያውቅና በብሔራዊ ቡድን ውስጥ ትልቅ ስኬት እንዲያስመዘግብ እንደረዳው በትልቁ ተወስቶለታል።

ከምሽቱ ጨዋታው ሰዓታት በፊት በጦርነት ለደቀቀችው ሀገር ትልቅ ታሪክ መፃፍ የሚያስችል ገድል ሊሰራ መቃረቡን በተመለከተ ጥያቄ ቀርቦለት የነበረው ኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ በሀገሪቱ የሊግ ውድድር መቋረጡ ትልቁ ፈተና እንደነበር ያስገነዘበበትን አስተያየት ሰጥቶ ህልሙ እንደሚሳካ ያለውን ተስፋ ገልፆ ነበር።

አብርሀም “በጣም አስቸጋሪ ጉዞ ነበር፤ ፈጣሪ ይመስገን በእስያ ዋንጫ እንጫወታለን። በየመን የእግር ኳስ ሊግ የሌለ በመሆኑ ትልቁ ፈተና እሱ ነበር። ተጫዋቾቼ ጨዋታ ያደርጉ የነበረው የብሔራዊ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታ ወይም የእስያ ዋንጫ ማጣሪያ ሲኖር ብቻ ነበር። ካለዚያ እግር ኳስ ጨዋታ የለም። 

“በእርግጥም ይህ ነገር በጣም አስቸጋሪ ነበር። 40 ተጫዋቾችን የያዘ ጊዜያዊ የልምምድ ስፍራ ላይ ከትሜ ነበር። ሶስት ወይም አራት ቡድኖችን ሰርቼ ብዙ የልምምድ ጨዋታዎችን አድርገናል። ከዛም ለእስያ ዋንጫ ማጣሪያ የሚሆነኝን ቡድን መረጥኩኝ። 

“ሁኔታው ለማጣሪያው በምትቀርፁት ስልት እና ታክቲክ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል። ተጫዋቾችን መምረጥ እና በአስተሳሰብ እና በአካል ብቃት ብቁ አድርጎ ወደጨዋታ በጥሩ ቅርፅ ማምጣት በጣም አስቸጋሪ ነበር።” ሲል ባለፉት ሁለት አመታት ትልቅ የአሰልጣኝነት ፈተና መጋፈጡን በዝርዝር አስረድቷል።

ይህ የኢንስትራክተር አብርሀም ጥረትም በምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ በጉልህ ታይቶ ቡድኑ ምንም አይነት ሽንፈት ሳይገጥመው ከሜዳው ውጪ ያስመዘገበውን ሶስት የአቻ ውጤት ጨምሮ በ 10 ነጥቦች ምድቡን በሁለተኛነት ፈፅሞ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ለሚደረገው የእስያ ዋንጫ ማለፍ ችሏል። .

ሶሪያ በመጨረሻ ባይሳካላትም በቅርቡ በአለም ዋንጫው ማጣሪያ እስከመጨረሻው መጓዝ የቻለችበትን አይነት ውጤት ባስታወሰ መልኩ ትልቅ ስኬትን ማስመዝገብ የቻለችው የመን የማጣሪያ ጨዋታዎቿን በሜዳዋ አለማድረጓ ሌላ ፈተናዋ የነበረ ቢሆንም ችግሩን በሚገባ በመቋቋም ለትልቅ ምዕራፍ በቅታለች።

የየመን ብሔራዊ ቡድን አባላት ከምሽቱ ጨዋታ መጀመር በፊት ማለፋቸውን ቀድመው ቢያረጋግጡም አብርሀም ከጨዋታው በፊት እንዳለው ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸውና ለሀገራቸው አዲስ ታሪክ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ባሳበቀ መልኩ ኔፓልን መርታት ችለው ገድ ሰባሪውን አዲስ ታሪክ ይበልጥ ያሳመረ ድል አስመዝግበዋል።

አብርሀምና በወጣቶች የተሞላው ስብስቡ አባላት አይናቸውን በሰፊው ከፍተው በቀጣዩ አመት ጥር ወር ላይ በሚደረገው የቀጠናው ትልቅ ውድድር ላይ ባነጣጠሩበት በዚህ ሰዓት የምሽቱ ውጤት የሀገሪቱን ሰላም ሙሉለሙሉ ባይመልስም በመጠኑም ቢሆን ውጊያው ጋብ እንዲል እንደሚረዳ ይጠበቃል።

ምክንያቱም ይህ ምንም የማይሳነው ለግድያ የሚፈላለጉ አካላትን ጭምር ወደአንድነት እና ሰላም ለማምጣት የማይዳግተው ቀዳሚው የአለም ተወዳጅ ስፖርት “እግር ኳስ” ነውና።

ሰላም ለየመንና ህዝቦቿ!! መልካም እድል ለአብርሀም እና ተስፈኛው ስብስቡ!! 

Advertisements