አነጋጋሪ የነበረው የሮናልዶ ኃውልት ዳግመኛ ተሰራ

በ2017 የዓለም ኮከቡን ክርስትያኖ ሮናልዶን የፊት ምስል ኃውልት የቀረፀው ኢማኑኤል ሳንቶስ በብዙዎች ዘንድ መዘባበቻ ሆኖ ነበር።

በወቅቱ ፓርቱጋላዊ ቀራፂ በመዳብ የሰራው እና በተጫዋቹ ስም በተሰየመው ማዲራ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መግቢያ ላይ እንዲተከል የተደረገው ጨርሶ ክርስቲያኖ ሮናልዶን የማይመስለው ኃውልት በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የቀልድ፣ የፌዝና የሽሙጥ መንስኤ መሆን ችሎም ነበር።

ይሁን እንጂ ኃውልቱ ከተሰራ አንድ ዓመት በኋላ ሳንቶስ በስፓርት ሚዲያው ብሊቸር ሪፓርት ክፍያ ኃውልቱን ዳግመኛ የመስራት ዕድል በቀረበለት መሰረት የሪያል ማድሪዱን ኮከብ ምስል በድጋሚ አስመስሎ ለመስራት ሙከራ አድርጓል።

በ2017 የተሰራው የሮናልዶ ኃውልት

“እኔ ሚዲያው እንዳቀረበኝ አይነት አለመሆኔን ለሰዎች ለማሳየት አሁንም የፊት ምስል ኃውልቱን ዳግመኛ እየሰራሁ ነው።” ሲል አርቲስቱ ተናግሯል።

ሁለተኛው የፊት ምስልን የሚያሳየው ኃውልት በተሻለ ሁኔታ የተስተካከለና ህይወት ያለው እንዲመስል ተደርጎ ቢሰራም፣ ከዚህ ቀደም በነበረው ኃውልት ላይ የነበረው የተጫዋቹ ፈገግታ ግን በአዲሱ ላይ የለም።

አዲሱ የሮናልዶ ኃውልት

“[የመጀመሪያውን ኃውልት] ውጤት ወድጄዋለሁ፤ እኮራበታለሁም። እናም ያን ዳግመኛ መስራት ካለብኝ ተመሳሳይ አድርጌ መስራቱንም የምወደው ነገር ነው።” ሲልም ሳንቶስ ጨምሮ ተናግሯል።

Advertisements