ባሎቴሊ በደቡባዊ ፈረንሳይ ድንቅ ብቃቱን እንዴት መልሶ ማግኘት ቻለ?

ማሪዮ ባሎቴሊ በቅርብ ጊዜያት በፈረንሳይ መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ይገኛል። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ስለተጫዋቹ በሚያዉቁት አይነት ባህሪ ግን አይደለም። ተከታዩ ፅሁፍም ስለተጫዋቹ ድንቅ ብቃት ሚስጥር በሰፊው ዳሷል

የርችት ማብራት፣ የከተማ ማዕከልን ማወክ፣ ያለተፈቀደ የእስር ቤት ጉብኝት፣ ከአስልጣኞችና የቡድን አጋሮቹ ጋር በልምምድ ላይ መደባደብ አሁን የለም። የጋዜጣዊ መግለጫ ስፍራ ሁካታ፣ እንዲሁም ወጣት ተጫዋቾች ላይ በዳርት ልምምድ መስራት የመሳሰሉት የከዚህ ቀደም የባላቶሊ አወዛጋቢ ተግባራትም አሁን የሉም።

ይልቁንስ ባሎቴሊ ከዚህ ቀደም ካስቆጠረው የግብ ብዛቶች የላቁ ግቦችን እያስቆጠረ ይገኛል።

ባላቶሊ ለፈረንሳዩ ክለብ ኒስ ባለፈው የውድድር ዘመን ባደረጋቸው 23 የሊግ 1 ጨዋታዎች 23 ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በዚህ የውድድር ዘመን ደግሞ በ21 ጨዋታዎች 14 ግቦችን በስሙ ማስመዝገብም ችሏል። ይህ ቁጥር ደግሞ የሚያንሰው ከኤዲሰን ካቫኒ፣ ረዳሜል ፈልካኦ እና ፍሎሪያን ታአይቪን ብቻ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ተጫዋቹ በኒስ ያስቆጠራቸው ግቦች ከዚህ ቀደም በተጫወተባቸው ክለቦች ላይ ካስቆጠራቸው የሊግ ግቦች የላቀ ነው። እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ የክለቡ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው።

ባላቶሊ በክለቡ የመጀመሪያ የውድድር ዘመን ኒስ ከ40 ዓመታት ወዲህ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በፈረንሳዩ ሊግ በሶስተኛ ደረጃ ማጠናቀቅ ችሏል። ምንም እንኳ ክለቡ በዚህ የውድድር ዘመን ደረጃው ወደስምንተኛነት ዝቅ ብሎ ቢገኝም ባላቶሊ ግን ኳስና መረብን ማገናኘቱን ቀጥሎበታል። ይህን ተግባሩን አስገራሚ የሚያደርገው ነገር ደግሞ የሉሲየን ፋቭሬው ቡድን ካደረጋቸው 14 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው ማሪዮ ባላቶሊ ተሰልፎ ባልተጫወተበት አንድ ጨዋታ ላይ ብቻ መሆኑ ነው። ሆኖም ቡድኑ አሸናፊ መሆን ባልቻለባቸው ጨዋታዎች ላይ ባላቶሊ ግቦችን ያስቆጥር ነበር።

ለአንድ የውድድር ዘመን በነበረው የኤሲ ሚላን የውሰት ቆይታው ጥሩ ጊዜን ሳያሰልፍ ወደሊቨርፑል በመዛወር በሊቨርፑል ለሁለት ዓመታት ብቃቱ ማሳየት ሳይችል ቀርቶ የነበረው ባሎቴሊ አበይት የአውሮፓ ክለቦችን እንደሚቀላቀል ታምኖ ነበር። ይሁን እንጂ የተጫዋቹ ቀጣይ ክለብ ማንም ባልጠበቀው ማንገድ የፈረንሳዩ ክለብ ኒስ ሆኗል።

ከሚዳ ውጪ በሚፈፅማቸው አወዛጋቢ ድርጊቶቹም ሮቤርቶ ማንቺኒ፣ ጆዜ ሞሪንሆ፣ ብሬንዳን ሮጀርስ እና የርገን ክሎፕ ያሉ የእግርኳሱ ዓለም ጉምቱ አሰልጣኞቹ የተጫዋቹን ብቃት ለማየት አልታደሉም።

ይሁን እንጂ ባሎቴሊ በ2016 ኒስን ከመቀላቀሉ ሶስት ወራት ቀድም ብለው ክለቡን የተቀላቀሉት ስዊዘርላንዳዊው አሰልጣኝ ፋቭሬ ግን እነዚያ አሰልጠኞቹ ያልተሳካላቸውን ነገር በማግኘት ስኬታማ መሆን ችለዋል። ምክኒያቱ ደግሞ አጥቂውን የትም ማሳካት ያልቻለውን ነገር አውጥቶ ማሳየት እንዲችል ማድረጋቸው ነው።

ፋቭሬ ሌሎች አሰልጣኞች ማድረግ ያልቻሉትን ባላቶሊን የመግራት ጥበብ ተክነውበታል

“ፋቭሬ በባላቶሊ ስኬታማ ነበሩ። ምክኒያቱም ባሎቴሊ ከዚህ ቀደም መድረስ ያልቻለበት ብቃት ላይ መድረስ ችሏል፡” ሲል ባሎቴሊ በኒስ ስለነበረው ቆይታ ኒስ-ማቲን በተሰኘው ጋዜጣ ላይ የፃፈው ዊሊያም ሃምበርሴት የተባለው ጋዜጠኛ ፅፏል። ፀኃፊው አክሎም “እንደሊቨርፑል ወይም ኤሲ ሚላን ባሉ ክለቦች ውስጥ ስኬታማ አለመሆን አንድ ነገር ነው። ነገር ግን በፈረንሳዩ ሊግ ትንሽ በሆነው ኒስ ክለብ ላይ ባይሳካለት የሚገርም አይደለም፤ ያበቃለትም ነበር።” ሲል ፅፏል።

ብዙውን ጊዜ ፋቭሬ እና ባሎቴሊ የሚጣጣሙ መስለው አይታዩም። ፋቭሬ ጠንክሮ በመስራትና አጨዋወት ይታወቃሉ። በአንፃሩ ባሎቴሊ የሚሰጠውን ትዕዛዝ መቀበል የማይወድ ነውጠኛ ተጫዋች ነው። ነገር ግን ለቡድኑ ስኬት ሁለቱም በየራሳቸው መንገድ ውጤታማ ሆነዋል። ባላቶሊ በልምምድ እና በጨዋታዎች ላይ በርካታ ተግባራትን ይፈፅማል። ፋቭሬ ደግሞ አጥቂው ከግቡ ፊትለፊት ስለሚፈፅማቸው ስህተቶች ለመናገር ወደኋላ የማይሉ ሰው ናቸው።

ፋቭሬ ኒስ በናፓሊ ተሸንፎ ከሻምፒዮንስ ሊጉ ውጪ ሲሆን “በጨዋታው ላይ በሚገባ ጠንካራ አልነበረም።” በማለት በባላቶሊ ላይ መራር ትችት ለመሰንዘር የሚፈሩት ነገር አልነበረም። ባላቶሊም ለተሰነዘረበት ትችት የአፀፋ ምላሽ ወይም መከላከያ ሃሳብ አልሰጠም።

ይህን የአሰልጣኙን ንግግር ተከትሎም የክለቡ አምበል የሆነው ብራዚላዊው ተከላካይ ዳንቴ ከፈረንሳዩ ኤስኤፍአር ስፖርት ጋር ባደረገው ቃለምልልስ “አሰልጣኙ የሆኑ ነገሮችን ይናገራል። ወደኋላ የሚለው ነገር የለም።” ሲል ገልፃ “‘ማሪዮ የማትሮጥ ከሆነ ከዚህ በኋማ ለእኔ አትጫወትም!’ ይሉታል። ሁኔታው በጣም የሚያስጨንቅ ነበር። ባላቶሊም ‘እንግዲያውስ ዩዜን ቦልትን ግዛው!’ ሲል ይመልሳል።” በማለት ተናግሯል።

ባለቶሊ በፌቭሬ አሰለጣጠን ደስተኛ በመሆኑ ባለፈው ክረምት በክለቡ ለመቆየት መወሰኑን ጥር ወር ላይ ለኒስ ይፋዊ ድረገፅ ተናግሯል። ተጫዋቹ የራሱ የባላቶሊ አሰልጣኝ ቢሆን ምን ብሎ ለራሱ እንደሚናገር ለቀረበለት ጥያቄም “ስለከፈልኩት ክፍያ የማቀርበውን ቅሬታ ለመቀነስ ጥረት አደርጋለሁ።” በማለት ተናግሮ “ነገሮች ሁልጊዜ ጥሩ ሲሆኑ ችግር አለ ማለት ነው። እንድ ሰው እግሬ ላይ ሲቆም እናደዳለሁ። እናም እኔም ይበልጥ መልሼ እቆምበታለሁ። ሰዎች ይበልጥ ስለእኔ ስህተት እንዲናገሩ አፈልጋለሁ። ምክኒያቱም ትምህርት የምትወስደው ከስህተቶችህ ነው።” ሲል ገልፅዋል።

ባሎቶሊ በቀደሙት ጊዜያት በመልበሻ ክፍል ውስጥ ብዙም በመልካም የሚታወስ ጊዜ አልነበረውም። ነገር ግን አብዛኞቹ ውጣት ተጫዋቾች በሆኑት የኒስ የቡድን አጋሮቹ ጋር ግን ጥብቅ ቁርኝት መፍጠር ችሏል።

ተጫዋቹ በ2016 በነሃሴ ወር ኒስን በተቀላቀለበት የመጀመሪያ ቀናት ለቡድን አጋሮቹ ወዳጅነቱን ለሚያጠናክር ስጦታ ለማበርከት 15,000 ዩሮ ወጪ አድርጓል። ከቀደሙት ጊዜያት በላቀም ግቦችን ሲያስቆጥር ከቡድን አ

በዚህ ላይ ከሜዳ ውጪ ባለው ህይወቱ ባለፈው ወር ከፍቅር አጋሩ ስሊያ የወንድ ልጅ አባት መሆን ችሏል። የልጁን ስምም ሊዮን (አንበሳ) ሲል ሰይሞታል። ተጫዋቹ ከቀደሞ የፍቅር አጋሩ ፒያ የተሰኘች የአምስት አመት ሴት ልጅም አለችው። በቅርቡ ከጣሊያኑ ኡኖ ከተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ባላቶሊ የባንክ ሰራተኛ እና የትርፍ ጊዜ ሞዴል የሆነችው ስሊያ ሰላሙን እንዲያገኝ እንዳገዘችው ገልፅዋል።

“የወጥ ብቃቴ ሚስጥር የሆነው ምንድን ነው? በቤቴ ውስጥ ካለ ሰው ሰላም ማግኘቴ ነው” ሲል ባሎቴሊ ተናግሮ “ሚስጥሩ ያለው እቤቴ ነው። በለፉት ጥቂት ዓመታት ከዚህ ቀደም የነበረብኝ የአካል ብቃት ችግር አልነበረብኝም። ብቃቴም ተሻሽሏል። ነገር ግን በቤቴ እንጂ በስራዬ ባገኘሁት ሰላም አይደለም።” ሲል ባሎቴሊ ገልፅዋል።

ባሎቴሊ በቤቱ ያገኘው ይህ ሰላምና መረጋጋት ደግሞ ከእሱ በፊት በክለቡ ስኬታማ እንደነበረው ሃቲም ቤናርፋ ሁሉ በኒስ እያገኘ ያለውን ስኬት የሚያንፀባርቅ ነው። የባህሪ ችግሮቹ ማነሳቸውም ትኩረቱን በሙሉ በሜዳው ላይ እንዲያደርግም አግዞታል።

“የሃገሪቱ ጋዜጦች ለኒስ የሚሰጡት ትኩረት አናሳ ነው። ስለዚህ ነገሮችን ከመጠን በላይ የሚያጋንን የሚዲያ ጫና የለበትም። ስለእሱ የሚሰጡ ፍርዶችም በሜዳ ላይ በሚያሳያቸው ነገሮች ላይ ብቻ ነው።” ሲሉ ኸምበርሴት ተናግረዋል።

“እሱ በጣሊያን እግርኳስ ላይ “የልጅ በጥባጭ” ነበር። ነገር ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት ያለውን ከፍ ያለ ብቃት ማሳየት ችሏል። ባሎተሊም ሆነ ኒስ ወደኒስ ሲመጣ የተጫወተውን ቁማር ብሎተሊ አሸናፊ ሆኗል።” ሲሉም ኸምበርሴት ጨምረው ተናግረዋል።

በመጪው ነሃሴ ወር 28 ዓመት የሚሞላው ባሎቴሊ ጣሊያን በ2014 የፊፋ ዓለም ዋንጫ በኡራጓይ 1ለ0 ተሸንፋ ከውድድሩ ውጪ በሆነችበት ጨዋታ ላይ በእረፍት ተቀይሮ ከወጣ ጊዜ አንስቶ ለሃገሩ አልተጫወተም።

ነገር ግን በሬኔስ ላይ ያስቆጠራት ለየት ያለች ግብ አጥቂው በዩሮ 2012 ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ በጀርመን ላይ ያስቆጠራትን ግብ እንዲታወስ ያደረገ ነበር። ወኪሉ ሚኖ ራዮላ ለጣላያኑ ራዲዮ 24 እንደተናገረው የጣሊያን ብሄራዊ ቡድን ጊዜያዊ አሰልጣኝ የሆኑት ሉዊጂ ዲ ቢያጂዮ ባሎቶሊን ወደብሄራዊ ቡድኑ ስለመመለስ ሊያስቡት እንደሚገባ የጠቆመ ሲሆን፣ የአዙሪዎቹ አምበል የሆነው ጂያንሉጂ ቡፎንም ባሎቴሊ ወደብሄራዊ ቡድኑ ዳግመኛ ተመልሶ መጫወት “እንደሚገባው”ም ገልፅዋል።

በክለቡ የሚኖረው የወደፊት እጣ ፈንታ አስመልክተውም የኒስ ክለብ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዣን-ፒየ ሪቬሬ ባላቶሊ በመጪው ክረምት ክለቡን የመልቀቁ ነገር ከፍ ያለ መሆኑን ለፈረንሳዩ አርኤምሲ ስፖርት ተናግረዋል። ባሎቴሊ ራሱ ዶሚኒካ ስፖርቲቫ ከተባለ ሚዲያ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ ወደጣሊያን ለመመለስ “ዝግጁ” መሆኑንና ወደጁቬንቱስ ወይም ናፓሊ ለመዛወር ንግግር እያደርገ መሆኑን ገልፅዋል። ራዮላም “ከበርካታ የእንግሊዝ እና የጣሊያን ክለቦች ጋር” ንግግር ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ለጣሊያኑ ጋዜጣ ካልቾ መርካቶ ተናግሯል።

በእርግጥ ባሎቴሊ ከአውሮፓ አበይት ክለቦች አንዱ በማምራት አሁን በፈረንሳይ እያሳየ የሚገኘውን ድንቅ ብቃት መቀጠል ይችል ይሆን? ይህ ጊዜ የሚመልሰው ቢሆንም ተጫዋቹ ግን ከሁለት ዓመት በፊት እንግሊዝን ከለቀቀ ወዲህ በብዙ መልኩ ለውጥ በማሳየት ኮከብ ተጫዋችነቱን እያስመሰከረ ይገኛል።

Advertisements