“ቫር ምቾት አልባ ወሲብ ነው።” – ሊዛራዙ

የቀድሞው የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቹ ቢክስኔቴ ሊዛራዙ በፈረንሳዩ የሊግ ዋንጫ ሞናኮ በፒኤስጂ ሽንፈት የደረሰበት ጨዋታ ላይ የተሻሩበትን ግቦች ተከትሎ በቪዲዮ የታገዘውን ዳኝነት (ቫርን) “ምቾት አልባ ወሲብ” ሲል ገልፃታል።

ሞናኮ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት ዋንጫውን ማሸነፍ በቻለው ፒኤስጂ የ3ለ0 ሽንፈት የደረሰበት ሲሆን፣ ለሽንፈቱ ደግሞ በቪዲዮ የታገዘው የዳኝነት ውሳኔ ወሳኙን ሚና ተጫውቷል።

የጨዋታው የመጀመሪያ ሁለት ግቦች በኤዲሰን ካቫኒ የተቆጠሩት የጨዋታው ዳኛ ክሌመንት ተርፒን የፍፁም ቅጣት ምቱን ለመስጠት ውሳኔ ላይ ለመድረስ ባለመቻላቸው የቪዲዮ እገዛው አስፈልጓቸው ነበር።

የቀድሞው የፈረንሳይ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ሊዛራዙ

እንዲሁም ጨዋታው 2ለ0 በመቀጠል ላይ እያለ የሞናኮው አጥቂ ራዳሜል ፋልካኦ ያስቆጠራት ግብ በዚሁ በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነት ውሳኔ እንድትሻር ሆናለች።

እናም ከፈረንሳይ ጋር የዓለም ዋንጫን እና የአውሮፓ ዋንጫን እንዲሁም ከባየርሙኒክ ጋር የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫም ማንሳት የቻለው ሊዛራዙ በቦርዶ በተደረገው ጨዋታ በእጅጉ ብስጭት ውስጥ ገብቷል።

የ48 ዓመቱ የቀድሞ ተጫዋች ጉዳዩን አስመልክቶም “በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነት (ቫር) ምቾት አልባ ወሲብ ነው። የደስታ ርችት በለኮስክበት ሰዓት እንድታቆም ይነገርሃል። እኔ በስታዲየሙ የተሰማኝ ስሜት እንደዚያ ነበር።

“የሞናኮ ደጋፊዎች በፋልካኦ ግብ ተደስተውና ጮቤ ረግጠው ነበር። ከዚያ ግን ሁሉንም ነገር እንድናቆም ተነገረን። አስቀያሚ ነገር ነበር። በጣም የሚያበሽቅ ነገርም ነበር።

“ያን ያህልም ፋይዳ ከሌለው ደጋፊዎች በምንም ነገር ላይ ተሳትፎ አይኖራቸውም። ደጋፊዎች ግን በጨዋታ ላይ መሳተፍ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ያን ተከልክለናል።

“ቪዲዮን በተሻለ ሁኔታ ልምጠቀምበት ይገባል። በስታዲየምም ሆነ በቴሌቭዥን ለምንመለከተው ሁሉንም ነገር ሊያብራራልንም ይገባል። ሁላችንም በአንድ የጨዋታ ክስተት ላይ ያለን ተሳትፎ ተመሳሳይ ነው።” ሲል ተናግሯል።

Advertisements