ድንቅ ብቃቱ ላይ የሚገኘው መሀመድ ሳላህ የዲዲየር ድሮግባን ሪከርድ ተጋራ

ግብፃዊው የሊቨርፑሉ የአጥቂ ተሰላፊ የሆነው መሀመድ ሳላህ ፓላስ ላይ አንድ ጎል ካስቆጠረ በኋላ የድሮግባን ሪከርድ ተጋርቷል።

በዘንድሮ የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ ድንቅ ብቃቱን ማሳየቱን የቀጠለው መሀመድ ሳላህ 29ኛ ጎሉን ክሪስታል ፓላስ ላይ አስቆጥሯል።

ተጫዋቹ ከሮማ ወደ ሊቨርፑል ከተዛወረ በኋላ በፍጥነት ከቡድኑ ጋር በመዋሀድ ለየርገን ክሎፑ ቡድን የፊት መስመር አስደናቂ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

የግራ እግሩ ባለቤት ትናንት ያስቆጠራት 29ኛ ጎሉ በፕሪምየርሊጉ የከፍተኛ ጎል አግቢነት ሩጫውን አጠናክሮ እንዲቀጥል አስችሎታል።

ይህ ብቻ ሳይሆን ሳላህ ዲድየር ድሮግባ 2019/2010 ላይ ለቼልሲ እየተጫወተ 29 የሊግ ጎሎችን በማግባት አንድ የአፍሪካ ተጫዋች በአንድ አመት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ውስጥ ያሳካው ከፍተኛ ጎል የማግባት ሪከርድን ተጋርቷል።

የሊጉ ውድድሮች ስድስት ጨዋታዎች የሚቀሩ በመሆኑ ተጫዋቹ ሌላ ጎል የማስቆጠር እድል ካገኘ የድሮግባን ሪከርድ የመስበር እድል ይኖረዋል።

ሳላህ እያሳየ ባለው አቋም በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ቢያንስ አንድ ጎል የማስቆጠር እድል እንደሚኖረው ስለሚታሰብ ተጫዋቹ አንድ የአፍሪካ ተጫዋች በእንግሊዝ ፕሪምየርሊግ ከፍተኛ ጎል በማስቆጠር ሪከርድ ለመጨበጥ ቀናቶችን መጠበቅ ብቻ ይበቃዋል።

ተጫዋቹ ሀገሩን ግብፅን ለአለም ዋንጫ እንድታልፍ ትልቅ አስተዋፅኦ በማድረጉ እንደ ጀግና እየታየ የሚገኝ ሲሆን በግብፅ የፕሬዝዳንት ምርጫም እስከ ሚሊየን የሚቆጠር ሰዎች እሱን እንደመረጡት ተነግሯል።

ግብጾቹ ወደ ራሺያ ሲያቀኑም የሚጓዙበት አይሮፕላን በስቲከር ከውጪ በመሀመድ ሳላህ ምስል ያሸበረቀ እንደሚሆንም ተሰምቷል።

Advertisements