ማንችስተር ዩናይትድ በ2018 የቅድመ ውድድር ዘመን በድጋሚ ወደ አሜሪካ እንደሚያቀና አሳወቀ

​ከ 2010 ጀምሮ ለአምስተኛ ጊዜ በሀገረ አሜሪካ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እንደሚያደርግ ያሳወቀው ማንችስተር ዩናይትድ በቆይታው የሚገጥማቸውን ቡድኖች ጭምር አሳውቋል።

የእንግሊዝ ፕሪምየርሊግን ከሰር አሌክስ ፈርጉሰን በኋላ ማንሳት ያልቻለው ዩናይትድ ዘንድሮም ቢሆን በጎረቤቱ ማን ሲቲ የበላይነት ተወስዶበታል።

በሊጉ ሊያጠናቅቅ የሚችልበት ከፍተኛ ውጤቱ ሁለተኛ ሲሆን በኤፍ ኤ ካፕ ደግሞ አሁንም በውድድሩ ውስጥ ይገኛል።

ቡድኑ በተለይ ከቻምፕየንስ ሊጉ በሲቪያ መሸነፉ ደጋፊዎቹን ያስቆጣ ሲሆን አመቱን በኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫ ወይንም ባዶ እጁን የማጠናቀቅ እድል ይኖረዋል።

ቡድኑ በቀጣዩ አመት ተጠናክሮ ለመቅረብ ከወዲሁም ተጫዋቾችን ለማዘዋወር ከጋሪዝ ቤል ጋር ስሙ በስፋት ተያይዞ ይገኛል።

ዩናይትድ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለ 2018/2019 ውድድር እንዲረዳው የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ለማድረግ ወደ አሜሪካ እንደሚያቀና አሳውቋል።

ቡድኑ ከ 2010 ጀምሮ በተደጋጋሚ ወደ አሜሪካ በማቅናት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተመልካቾች ማግኘት ችሏል።

እስከ አሁን በአሜሪካ 1.3 ሚሊየን የሚሆኑ ተመልካቾች የቀዮቹን ሰይጣኖች ጨዋታ የተመለከቱ ሲሆን በተለይ 2014 ላይ ማድሪድን ሲገጥሙ 109 ሺ ተመልካቾች በስታድየም ተገኝተው ተከታትለውታል።

በአሜሪካው ቆይታው በፈረንጆቹ አቆጣጠር ሀምሌ 19 በአሪዞና ፎኒክስ ስታድየም ከሜክሲኮው ክለብ አሜሪካ ጋር ሲጫወት በመቀጠል ወደ ሳንታክላራ በማቅናት ሀምሌ 22 ላይ በሌቪ ስታድየም ከሳን ሆዜ ጋር ይጫወታል።

ቡድኑ በቀጣይም ሌሎች የጨዋታ መርሀግብሮችን እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል።

Advertisements