ቬንገር ስለሚክሂታሪያን የጉዳት መጠን ተናገሩ

አርሰን ቬንገር ሂነሪክ ሚክሂታሪያን አርሰናል የፊታችን እሁድ ከሳውዛምፕተን ጋር ከሚያደረገው ጨዋታ ውጪ መሆኑን ገልፀው፣ ነገር ግን በአርመናዊው ተጫዋች የጉልበት ጉዳት መጠን ምን ያህል እንደሆነ እንደማያውቁም ተናግረዋል።

የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ አማካኝ አርሰናል ሃሙስ ምሽት በዩሮፓ ሊግ ሲኤስካ ሞስኮን በአሮን ራምሴ እና አሌክሳንደር ላካዜቲ ግቦች 4ለ1 ማሸነፍ በቻለበት ጨዋታ በ61ኛው ደቂቃ በገጠመው ጉዳት እያነከሰ ከሜዳው ለመውጣት ተገዷል።

ቬንገር ከጨዋታው በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃለምልልስ እንደተናገሩት ከሆነ በጥር ወር ክለቡን የተቀላቀለው ተጫዋች የጉልበት ጉዳት እንደገጠመውና እሁድ ቅዱሳኑ ወደኤመራት አምርተው ከሚያደረጉት ጨዋታ ውጪ መሆኑን ገልፀዋል።

“[ሚክሂታሪን] የጉልበት ጉዳት አለበት።” ሲሉ ቬንገር ተናግረዋል።

“ጉዳቱ ምን ያህል መጥፎ እንደሆነ አለወቅንም። ነገ (አርብ ) ጠዋት ይህን የምናጠራ ይሆናል። ከእሁዱ ጨዋታ ውጪ መሆኑ ግን እርግጥ ነው።” ሲሉም አሰልጣኙ ጨምረው ገልፀዋል።

በሌላ በኩል ቬንገር በዩሮፓ ሊግ ውድድር ላይ መደበኛ የግብ ጠባቂነት ሚና የነበረው ዴቪድ ኦስፒና የቁርጭምጭሚት ጉዳት የገጠመው መሆኑን ተከትሎ ለፒተር ቼክ ለሁለተኛ ጊዜ በዩሮፓ ሊግ ጨዋታ ላይ እንዲሰለፍ ዕድል ሰጥተውታል።

እናም የመድፈኞቹ አሰልጣኝ ኮሎምቢያዊ ግብ ጠባቂ ከመልሱ ጨዋታ ውጪ መሆኑን ተናግረዋል።

“ዛሬ የህክምና ምርመራ ማረጋገጫ አግኝተናል።” ሲሉ ቬንገር ተናግርው “እሱ [ኦስፒና] ከ2-3 ሳምንታት ከጨዋታ ይርቃል።” በማለት ገልፀዋል።

Advertisements