የሲምባ እና የያንጋ ባላንጣነት ወላይታ ድቻን ተጠቃሚ ያደርገው ይሆን?

ሁለቱ የታንዛኒያ ታላላቅ ቡድኖች የሆኑት የያንግ አፍሪካ[ያንጋ] እና የሲምባ ባላንጣነት ወላይታ ድቻ ከሜዳው ውጪ ሊያገኝ የሚችለው ጠንካራ ድጋፍ ተጠቃሚ ያደርገው ይሆን?

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅዳሜ ከሰአት የታንዛኒያ ያንግ አፍሪካ ከኢትዮጵያው ወላይታ ድቻ ጋር የሚያደርገው የሜዳው ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።

በውድድሩ ላይ እንግዳ ቢሆንም ሰፊ ልምድ ያለውን ዛማሌክን አንገት አስደፍቶ በማሸነፍ መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው ወላይታ ድቻ ሌላ ታሪክ ለማስመዝገብ ወደ ጎረቤት ታንዛኒያ አቅንቷል።

ቡድኑ በከፍተኛ መነቃቃት ላይ የሚገኝ ሲሆን ይኸው መነቃቃት በሀገር ውስጥ ውድድር ላይ በመቀጠል የሊጉን መሪ ደደቢትን ሲያሸንፍ አዲስ አሰልጣኝ ከቀጠረው መከላከያ ጋር አቻ ተለያይቷል።

በዚህም መሰረት በሊጉ ሰንጠረዥ ላይ በ 17 ጨዋታዎች 23 ነጥብ በመሰብሰብ በዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የታንዛኒያው ታላቁ ቡድን የሆነው ያንግ አፍሪካ በበኩሉ በአፍሪካ መድረክ ከድቻ የተሻለ ልምድ ያለው በመሆኑ ወደ ምድብ ድልድሉ እንደሚገባ የቅድሚያ ግምት አግኝቷል።

ቡድኑ በሀገር ውስጥ ውድድር ላይ ከዘውትር ተቀናቃኙ እና ከባላንጣው ሲምባ ጋር አንገት በአንገት በመያያዝ የሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ተከታትለው ተቀምጠዋል።

የሁለቱ ቡድኖች ፉክክር ጥቂት ጨዋታዎች ብቻ የቀሩት የታንዛኒያ ፕሪምየርሊግ አሸናፊ ሆኖ ለማጠናቀቅ እንደ ሌሎቹ አመታት ሁሉ አንዱ የአንዱን ሽንፈት እየናፈቁ ቀጥለዋል።

የተቃራኒ ቡድን በመደገፍ ነጥብ አስጥሎ ለመፈንጠዝ የሚደረገው ሽኩቻ በስፋት በሚያይበት የያንጋ እና የሲምባ ባላንጣነት ባለፉት አመታትም በአፍሪካ መድረኮች ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች ላይም ታይተዋል።

ይህም ያንግ አፍሪካ በሜዳው ያደረጋቸው ጨዋታዎች የሲምባ ደጋፊዎች ለእንግዳው ቡድን ድጋፍ በመስጠት ሲያበረታቱ መመልከት አዲስ ነገር አይደለም።

ይኸው ሂደት ቅዳሜ ከሰአት ያንጋ በሜዳው ከወላይታ ድቻ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ የኢትዮጵያው ተወካይ ከሲምባ ደጋፊዎች ጠንካራ ድጋፍ እንደሚያገኝ ይጠበቃል።

ይህ ከሜዳ ውጪ የሚገኝ ድጋፍ ደግሞ እንግዳው ቡድን  የጨዋታው የመጀመሪያ 30 ደቂቃዎች ላይ ጎል ሳይቆጠረበት አጀማመሩን ካሳመረ ባለሜዳዎቹን ጫና ውስጥ ሊያስገባ እንደሚችል ይጠበቃል።

ያንጋ በውድድሩ ላይ የተሻለ ልምድ ያለው በመሆኑ የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት ያገኘ ሲሆን ይህ ደግሞ ቡድኑን ጫና ውስጥ ሊከተው የሚችል ሌላ ተጨማሪ ጉዳይ መሆኑ የማይቀር ነው።ይህ ደግሞ ድቻዎች ዛማሌክን እንዳሸነፉት ሁሉ በጎ ነገር ሊፈጥርላቸው ይችላል።

ሁለቱ ቡድኖች 60 ሺ በሚይዘው በዳሬሰላም ብሔራዊ ስታድየም በሚያደርጉት የነገው ጨዋታ ባለሜዳዎቹ አራት ወሳኝ ተጨዋቾቻቸውን አያገኙም።

ኦብሬ ቺርዋ፣ጁማ ሰይድ፣ኬልቪን ዮንዳኒ እና ፓፒ ቲሺሺምቢ በቅጣት ምክንያት ጨዋታው ላይ ተሳትፎ አይኖራቸውም።

ከወላይታ ድቻ ደግሞ ሁለት ተጫዋቾች [እሸቱ መና እና ተክሉ ተስፋዬ]በቅጣት ከጨዋታው ውጪ ናቸው።

የሁለቱ ቡድኖች የደርሶ መልስ አሸናፊ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወደ ምድብ ድልድሉ ውስጥ መግባቱ ያረጋግጣል።

ያንጋ በካፍ ቻምፕየንስ ሊግ ላይ በቦትስዋናው ታውንሺፕ ሮለርስ ተሸንፎ ወደ ምድብ ድልድሉ መግባት ባለመቻሉ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ለመሳተፍ መገደዱ ይታወሳል።

Advertisements