“እኛ ተጫወትን ነገርግን ያንጋ አሸነፈ”- ወንደሰን ገረመው


ወላይታ ድቻ ወደ ታንዛኒያ አቅንቶ በያንግ አፍሪካ የ 2-0 ሽንፈት ካጋጠመው በኋላ ግብጠባቂው ወንደሰን ገረመው “እኛ ተጫወትን ነገርግን እነሱ አሸነፉ” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወደ ምድብ ድልድል ለማለፍ የታንዛኒያውን ያንግ አፍሪካ የገጠመው ወላይታ ድቻ 2-0 ተሸንፏል።

ወላይታ ድቻ የግብፁን ዛማሌክ ከውድድሩ በማስወጣት ለዛሬው ጨዋታ የደረሰ ሲሆን ያንግ አፍሪካ በበኩሉ በካፍ ቻምፕየንስ ሊግ በቦትስዋናው ሀጀጀከ ተሸንፎ ወደ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫው መቀላቀሉ ይታወሳል።

ዛሬ 10:00 በታንዛኒያ ብሔራዊ ስታድየም ባደረጉት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ባስቆጠሩት ጎል በጊዜ ቢመሩም ድቻ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ እንቅስቃሴ አድርጓል።

እንግዳዎቹ ምንም እንኳን ጎል ለማግባት ያደረጉት ጥረት ውስን የነበረ ቢሆንም የነበራቸው እንቅስቃሴ ግን መልካም የሚባል እንደነበረ ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ይህን ያጠናከረ አስተያየት ደግሞ የወላይታ ድቻው ገብ ጠባቂ ወንደሰን ገረመው ሰጥቷል።

ከዛማሌክ ጋር በነበረው ጨዋታ የመለያ ምት በማዳን ወላይታ ድቻ ለዛሬው ጨዋታ እንዲደርስ ትልቅ ሚና የተጫወተው ወንደሰን “እኛ ተጫወትን ያንግ አፍሪካ አሸነፈ” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

ግብ ጠባቂው አያይዞ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ከባድ ቢሆንም ከዚህ ቀደም የያንግ አፍሪካን አጨዋወት እንደማያቁት ነገር ግን አሁን ቡድኑን በመመልከታቸው ለቀጣዩ ጨዋታ ማሸነፍ እንዲችሉ እንደሚያደርጋቸው ገልጿል።

ወንደሰን ጨምሮ “ዛሬ ጥሩ ተጫውተናል በሜዳችን የምናደርገው ጨዋታም ዛሬ ካደረግነው የተሻለ ስለምንጫወት አሸንፈን እናልፋለን።” ሲል ምላሹን ሰጥቷል።

Advertisements