ማን ሲቲ ከ ሊቨርፑል | የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ

ሊቨርፑል የፔፕ ጋርዲዮላውን ማንችስተር ሲቲን በመጀመሪያው ዙር በአንፊልድ 3ለ0 በሆነ ውጤት በማሸነፉ አንድ እግሩን አስቀድሞ ወደሻምፒዮንስ ሊጉ የግማሽ ፍፃሜ ዙር በማስገባት ወደኢትሃድ ስታዲየም ተጉዞ የመልሱን ጨዋታ የሚያደረግ ይሆናል።

ማንችስተር ሲቲዎችም ጨርሶ ተስፋ ባለመቁረጥ ስሜት የየርገን ክሎፑን ቡድን ውጤት ለመቀለበስ የሚጫወቱም ይሆናል።

በዋንጫ ውድድሮች ላይ የትኛውም አይነት ውጤት ሊከስት መቻሉን ከግምት ውስጥ በማስገባትም ውሃ ሰማያዊዎቹ በምሽቱ ጨዋታ አንዳች አዎንታዊ ታላቅ ተስፋን በልባቸው ሰንቀው ወደግማሽ ፍፃሜው ማሳለፍ የሚያስችላቸውን ውጤት ለማግኘት የሞትሽረት ትግል እንደሚያደርጉ ይጠበቃል

የቡድኖቹ ዜናዎች

ማንችስተር ሲቲ

ሰርጂዎ አጉዌሮ ገጥሞት ከነበረው የጉልበት ጉዳት ቅዳሜ በማንችስተር ደርቢ ጨዋታ ላይ የተጫወተ ሲሆን፣ ከሊቨርፑል ጋር በሚደረገው በዚህ ጨዋታ ላይም እንደሚሰለፍ ይጠበቃል። ከዩናይትድ ጋር በተደረገው ጨዋታ የመጀመሪያ ተሰላፊ ያልነበሩት ኬቨን ደብሩይኔ እና እና ካይል ዎከርም በዚህ ጨዋታ የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ እንደሚገቡ ይጠበቃል። ቪንሰንት ኮምፓኒ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ሶስት ጨዋታች ላይ ሊሰለፍ መቻሉ እርግጥ አይደለም። ይህ ማለት ደግሞ በምትኩ ገጥሞት ከነበረው ቀላል ጉዳት ያገገመው ጆን ስቶንስ ለዛሬ ምሽቱ ጨዋታ የመጀመሪያ ተስላፊነት ሚና ጥሪ ሊቀርብለት ይችላል።

ሊቨርፑል

ኤምሬ ቻን እና ጆርዳን ሄንደርሰን ከማንችስተር ሲቲ ጋር በሚደረገው በዚህ ጨዋታ ላይ የማይሰለፉ በመሆናቸው ሊቨርፑል የመሃል አማካኝ ችግር አለበት። ይሁን እንጂ ከኤቨርተን ጋር በተደረገው የቅዳሜው ጨዋታ በዚህ ስፍራ ላይ ተጫውቶ ድንቅ ብቃት ማሳየት የቻለው ጆርጂዮ ዊይናልደም በዚህ ጨዋታ ላይም ቦታውን እንደሚያስጠብቅ ይታመናል። ባለፈው ሳምንት ከሲቲ ጋር በተደረገው ጨዋታ ቀላል የብሽሽት ጉዳት ደርሶበት የነበረው እና በመርሲሳይዱ ደርቢ ጨዋታ ላይ እረፍት የተሰጠው መሐመድ ሳላህ ወደሜዳ እንደሚመለስ ይጠበቃል። በቅዳሜው ጨዋታ እረፍት እንዲወስዱ ተደረገው የነበሩት ሮበርትሰን፣ አሌክሳንደር-አርኖልድ፣ ፊርሚኖ፣ እና ኦክስሌድ-ቻምበርሌንም በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ እንደሚካተቱ ይጠበቃል።

ግምታዊ አሰላለፎች

የሁለቱ ቡድኖች ቁጥራዊ እውነታዎች

  • ሊቨርፑሎች ለመጨረሻ ጊዜያት ባደረጓቸው ያለፉት 7 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች በ6ቱም ላይ ቢያንስ 3 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።
  • ሊቨርፑሎች ካደረጓቸው ያለፉት 7 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች በ6ቱ መረባቸውን አላስደፈሩም።
  • ሊቨርፑሎች ላደረጓቸው ያለፉት 13 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች አንድም ሽንፈት አልገጠማችውም።
  • ማንችስተር ሲቲዎች ካደረጓቸው ያለፉት 7 የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች በ6ቱ ላይ ከ2.5 ግቦች በላይ ማስቆጠር ችለዋል።
  • ማንችስተር ሲቲዎች በሁሉም ውድድሮች ላይ በሜዳቸው ከሊቨርፑሎች ጋር ለመጨረሻ ጊዜያት ካደረጓቸው ያለፉት 7 ጨዋታዎች በስድስቱ ላይ ከ2.5 በላይ ግቦችን አስቆጥረውባቸዋል።
Advertisements