ስህተት / የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር ኤልኒኒ በሳውዝአምፕተኑ ጨዋታ የተመለከተውን ቀይ ካርድ አነሳ

የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር አርሰናል 3-2 በሆነ ውጤት ሳውዝአምፕተንን በረታበት ያሳለፍነው እሁድ ጨዋታ ላይ ግብፃዊው ሞሀመድ ኤልኒኒ የተመለከተውን የቀይ ካርድ ቅጣት አንስቶለታል።  

የመድፈኞቹ አማካኝ በእሁድ አመሻሹ ፍልሚያ ከቅዱሶቹ ተከላካይ ሴድሪክ ጋር በተፈጠረው ግብግብ እጁን በማንሳቱ በጨዋታው ዳኛ አንድሬ ማሪነር የቀጥታ ቀይ ካርድ ተመልክቷል። 

በዕለቱ የሳውዝአምፕተኑ ሌላኛ ተከላካይ ጃክ ስቴፈንስም በጨዋታው መጠናቀቂያ አቅራቢያ ከጃክ ዊልሻየር ጋር በፈጠረው እሰጣ ገባ ከሜዳ ተወግዷል። 

በእሰጣገባ የታጀበውን የእሁዱን ጨዋታ ሂደት የመረመረው ነፃ የግልግል አካል የሰጠውን ውሳኔ ተከትሎም የእንግሊዝ እግር ኳስ ማህበር ውሳኔው ስህተት እንደሆነ በመግለፅ የኤልኒኒን ቅጣት አንስቶለታል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አርሰን ቬንገር በሰጡት መግለጫም አማካኛው በተመለከተው ቀይ ካርድ መደነቃቸውንና በውሳኔው ላይ ይግባኝ እንደሚያቀርቡ መግለፃቸው አይረሳም።  

Advertisements