“የፍፁም ቅጣት ምት ወይስ ..?” ማይክል ኦሊቨር ከጁቬንቱስ ካምፕ ጠንካራ ትችት ቀረበባቸው

ጁቬንቱስ ወደ ስፔን አቅንቶ በመጀመሪያ ዙር ተጠናቀቀ የተባለለትን ጨዋታ በሳንቲያጎ በርናባው ሶስት ጎል አግብቶ ነፍስ ቢዘራም 93ኛ ደቂቃ ላይ እንግሊዛዊው ዳኛ ማይክል ኦሊቨር ለማድሪድ የሰጡት የፍፁም ቅጣት ምት ከጣሊያኖቹ ጠንካራ ትችት ቀርቦባቸዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ፊፋ በ 2018 የአለም ዋንጫ ላይ የሚዳኙትን ዳኞች ይፋ ሲያደርግ እንግሊዛዊያን አለመካተታቸው መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

በተለይም በፕሪምየርሊጉ ትላልቅ ጨዋታዎችን በማጫወት የሚታወቀው ወጣቱ ማይክል ኦሊቨር መቅረት እንዳልነበረበት ብዙዎች ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

ነገርግን በቅርቡ በፕሪምየርሊጉ የታዩ የዳኝነት ስህተቶች ፊፋ እንግሊዛዊያን ዳኞችን አለማካተቱ ትክክለኛ መሆኑን አስረግጠው የሚናገሩ በዝተዋል።

ምሽት ላይ ማድሪድ ጁቬንቱስን ባስተናገደበት ጨዋታ ላይም እንግሊዛዊው ማይክል ኦሊቨር በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ለባለሜዳዎቹ የሰጡት የፍፁም ቅጣት ምት ለትችት አጋልጧቸዋል።

ዳኛው መድሂ ቤናሺያ ሉካስ ቫስኩዌዝ ላይ ጥፋት ሰርተሀል በማለት የሰጡት አጨቃጫቂ የፍፁም ቅጣት ምት ባለሜዳዎቹን ወደ ግማሽ ፍፃሜ እንዲያቀኑ አድርጓቸዋል።

ይኸው ውሳኔ በተለይ ከጁቬንቱስ ካምፕ ዳኛው ላይ ጠንካራ ትችት እንዲቀርብ አስገድዷል።

ግብጠባቂው ቡፎን “እሄ ዳኛ ልብ የለውም።ልቡ ያለው የቆሻሻ መጣያ እቃ ውስጥ ነው።አንዳንድ ጊዜ የጨዋታው አስፈላጊነት መረዳት አለብህ ይህ ካልሆነ ግን መገኘት ያለብህ ሜዳ ውስጥ ሳይሆን ኮካ እና ቺፕስ ይዘህ ከተመልካች መሀል ነው” ሲል ወርፎታል።

የጁቬንቱስ ፕሬዝዳንት የሆኑት አንድሪያ አግኒሊ ቡድናቸው ላይ መድሎ እንደደረሰ በማሳወቅ “ሙሉ ለሙሉ ቀውስ”ብለውታል።”የፀረ ጣሊያን”አጀንዳ ሲሉም የአውሮፓ እግርኳስ ማህበርን ተችተዋል።

ብዙ አስተያየት ሰጪዎች እንቅስቃሴው ንክኪ ቢኖረውም ጨዋታው ሊጠናቀቅ ከመቃረቡ አንፃር ውሳኔው ለፍፁም ቅጣት ምት በቂ እንዳልነበረ ተናግረዋል።

ውድ የድረገፃችን አንባቢዎች የእናንተስ እይታ እንዴት ነበር?የፍፁም ቅጣት ምቱ ያሰጣል ወይስ አያሰጥም?


Advertisements