ሊቨርፑል ከ ሮማ፡ የከዚህ ቀደም ግንኙነታቸውና ስለድልድሉ የተሰጡ አስተያየቶች

ሊቨርፑል በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ የዕጣ ድልድል የጣሊያኑን ኤኤስ ሮማን ለመግጠም ተደልዷል። ተከታዩ ፅሁፍም የሁለቱን የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ክለቦች የከዚህ ቀደም ግንኙነት እና ድልድሉን አስመልክተው የተሰጡ አስተያየቶችን ተመልክቷል።

ቀዮቹ በሩብ ፍፃሜው ማንችስተር ሲቲድን በደርሶ መልስ 5ለ1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል።

በሌላ በኩል የሴሪ አው ክለብ ሮማ ደግሞ በባርሴሎና የደረሰበትን የ4ለ1 ሽንፈት በሮም በመቀልበስ 3ለ0 በሆነ ውጤት አሸንፎ ከሜዳው ውጪ ባስቆጠርው ግብ ታግዞ ግማሽ ፍፃሜውን መቀላቀል ችሏል።

የሁለቱ ክለቦች የከዚህ ቀደም ግንኙነት

ሁለቱ ክለቦች በአውሮፓ አበይት መድረኮች (በዩሮፒያን ካፕ፣ በዩሮፓ ሊግና በሻምፒዮንስ ሊግ ውድድሮች) ላይ እርስ በእርስ በተገናኙባቸው ጨዋታዎች ሊቨርፑል 3 ጊዜ አሸናፊ ሲሆን፣ ሮማ ደግሞ 1 ጊዜ በማሸነፍ ቀሪ 1 ጨዋታ ላይ ደግሞ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል።

ሮማ ከ ሊቨርፑል፡ 1-1 የአውሮፓውያኑ ዋንጫ( እ.ኤ.አ. 1984)
ሮማ ከ ሊቨርፑል፡ 0-2 ዩኤፋ ካፕ (እ.ኤ.አ. 2001)
ሊቨርፑል ከ ሮማ፡ 0-1 ዩኢኤፋ ካፕ (እ.ኤ.አ. 2001)
ሮማ ከ ሊቨርፑል፡ 0-0 ሻምፒዮንስ ሊግ (እ.ኤ.አ. 2001)
ሊቨርፑል ከ ሮማ፡ 2-0 ሻምፒዮንስ ሊግ (እ.ኤ.አ. 2002)

የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታው መቼ ይደረጋል?

በሁለቱ ክለቦች መካከል የሚደረገው የደርሶ መልስ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ የመጀመሪያው ሚያዝያ 16፣ 2010 ዓ.ም ሲደረግ የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ሚያዝያ 26፣ 2010 ዓ.ም በሮም የሚደረግ ይሆናል።

ስለድልድሉ የተሰጡ አስተያየቶች

የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ፡ “ከዚህ በኋላ የሆነ ነገር መናገር እንዳለብኝ ስለማውቅ የተሰማኝን ለመረዳት ጥረት አድርጌያለሁ። ነገር ግን የተረዳሁት “እሰይ እንኳን ሮማ ሆነ። ባየርን እና ሪያል ማድሪድን ባለማግኘታችን ፈጣሪ ይመስገን።” የሚል ስሜት አይደለም። ወይም ሌላ ተመሳሳይ ስሜት አይደለም።

“ነገሩ የዕጣ ድልድል ብቻ ነው። በጣም አስደሳች እንደሆነ አውቃለሁ። ነገር ግን ጥሩው ነገር ተጋጣሚያችን ማንም ቢሆን ወሳኙ ነገር አሁንም በውድድሩ ላይ የምንገኝ የመሆናችን ዜና ነው። እግርኳስ በመሆኑ አሁንም እድል እንዳለ መናገር ይኖርብኛል። ስለዚህ አሁንም ሮማን የምንገጥምበት ዕድል አለ።

“ነገር ግን ድልድሉ ቀላል ነው ብሎ የሚያስብ ካለ ይህን ሰው ም ልለው አልችልም። ምክኒያቱም እነሱ ከባርሴሎና ጋር ያደረጉትን ሁለት ጨዋታዎች አልተመልከተም። የመጀመሪያው ውጤት 4ለ1 ነበር። ደግሞም ጨዋታው ከጥሩውና መሲን ከያዘው ክለብ ጋር ነበር። በሁለተኛው ጨዋታ ላይ ያደረጉት ነገር ደግሞ በእጅጉ አስደናቂ ነበር። አራት ወይም አምስት ለዜሮ ሊያሸንፉም ይችሉ ነበር።
እኔንም በእጅጉ ደንቆኛል።

“ተሳክቶላቸዋል። በእዚህ ላይ ምንም ችግር የለብንም። አሁን የምናስበው ስለመጀመሪያ ጨዋታችን ነው፡”

የሮማው የስፖርቲንግ ዳይሬክተር ሞንቺ፡ “ለረጅም ጊዜያት ማግኘት ያልቻለነውን ደስታ ለማግኘት መቻላችን ትልቅ ዕድል የማግኘት ያህል ስሜት አለው።

“ነገር ግን አስቸጋሪም ነው። ምክኒያቱም ሊቨርፑል እጅግ በጣም ጠንካራ ቡድን ነው።

“ስለራሳችን ማሰብ እና በባርሴሎና ላይ መፍጠር የቻልነውን መድገም የግድ ይለናል።”

ሮማ በይፋዊ የትዊተር ገፁ ለቀድሞ ተጫዋቹ መሐመድ ሳላህ፡ “ለ180 ደቂቃዎች ተቃራኒ እንሆናለን። ነገር ግን ምንም ነገር ቢፈጠር ወዳጅነታችን ለእድሜ ልክ ዘላቂ ይሆናል። ዳግመኛ ልናይህም እንናፍቃለን። “

Advertisements