ባለ ትልቁ ጆሮ የቻምፕየንስ ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ያልቻሉ ምርጥ 11 ተጫዋቾች እነማን ናቸው?

የቻምፕየንስ ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ሳይችሉ የእግርኳስ ህይወታቸውን የቋጩ እንዲሁም ጫማቸውን ለመስቀል የተቃረቡ ከዋክብቶችን የያዘ ምርጥ 11 ተጫዋቾች የያዘ ቡድን ይፋ ተደርጓል።

1) ግብ ጠባቂ – ጂጂ ቡፎን

ቡፎን ባሳለፋቸው ረጅም የእግርኳስ ህይወቱ ባለ ትልቁን ጆሮ ዋንጫ ለማንሳት ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ማሳካት አልቻለም።

ቡፎን ባለፈው አመት እና ዘንድሮ በተከታታይ በሪያል ማድሪድ ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ ሆኗል።ግብጠባቂው ዘንድሮ ጁቬንቱስ የቻምፕየንስ ሊግ ዋንጫን ማንሳት የማይችል ከሆነ ጫማውን እንደሚሰቅል ማሳወቁን ተከትሎ ዘንድሮ የመጨረሻው ተሳትፎ ሲሆን ውድድሩንም በአሳዛኝ ሁኔታ በቀይ ካርድ በመውጣት ተሰናብቶታል።

ቡፎን በፍፃሜ ጨዋታ ለሶስተኛ ጊዜ በማድሪድ ከተሸነፈ በኋላ

1997 ላይ በወጣትነቱ ከፓርማ ጋር እንዲሁም ከአሮጊቷ ጋር በተከታታይ በተሳተፈበት መድረክ ከጁቬንቱስ ጋር ሶስት ጊዜ ለፍፃሜ ቢደርስም ዋንጫውን ለማንሳት ግን አልታደለም። 

ጂጂ ቡፎን በአመቱ መጨረሻ ላይ ረጅም አመት ከቆየበት የእግርኳስ ህይወቱ ጡረታ እንደሚወጣ ይጠበቃል።

2)ተከላካይ – ሊሊያም ቱራም

በጠንካራ ሁለገብ ተከላካይነቱ የሚታወቀው ፈረንሳዊው ሊሊያም ቱራም እንደ ቡፎን ሁሉ ከፓርማ ጀምሮ የነበረው የአውሮፓ ቆይታ የቻምፕየንስ ሊግ ዋንጫን ለማግኘት ከመቃረብ ውጪ ማንሳት አልቻለም።

ቱራም በጁቬንቱስ

2003 ላይ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ በኦልድትራፎርድ ለጁቬንቱስ እየተጫወተ ከሚላን ጋር እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ ቢያደርጉም ዋንጫውን ለሚላን አሳልፈው የሰጡበት አጋጣሚ ለቱራም የውድድሩ መጥፎ ትዝታው ነው።

3) ተከላካይ – ፋቢዬ ካናቫሮ

ቁመቱ እንደ ሌሎች የመሀል ተከላካዬች ረዘም ያለ ባይሆንም የአየር ኳስ የሚከላከልበት መንገድ አስገራሚ እንደነበር ይታወሳል።

ካናቫሮ ጣሊያን ካፈራቻቸው ተከላካዬች ውስጥ በጠንካራነቱ እና በእልህ አስጨራሽ ፍልሚያው ይለያል።

ጠንካራው ፋቢዮ ካናቫሮ

ይኸው የቀድሞ ተከላካይ ሪያል ማድሪድን ጨምሮ በተላላቅ የአውሮፓ ክለቦች ውስጥ ቢሳተፍም ባለ ትልቁን ጆሮ ዋንጫ ለማንሳት አልቻለም።

ተጫዋቹ በውድድሩ ለፍፃሜ ቀረብ ያለበት ወቅት ለኢንተር ሚላን እየተጫወተ በግማሽ ፍፃሜው በከተማው ተቀናቃኝ ሚላን ከሜዳ ውጪ ጎል ምክንያት ከውድድሩ ውጪ የሆነበት ነው።

4) ተከላካይ – ጆርጂዮ ቼሊኒ

ቼሊኒ እንደ ቡፎን ሁሉ ለፍፃሜ ከመቅረብ ውጪ ዋንጫን ለማሸነፍ ያልታደለ ተጫዋች ሆኗል።

ጠንካራ ተከላካይ የሆነው ተጫዋች ከእድሜው መግፋት ጋር ይህን ዋንጫ የማንሳት ወቅቱ እያለፈ ይገኛል።

ቼሊኒ እሮብ ምሽት በማድሪድ ከተሸነፉ በኋላ

2015 ላይ በፍፃሜ በባርሴሎና ሲሸነፉ በጉዳት አልተሰለፈም።ባለፈው አመት ደግሞ በማድሪድ ሲሸነፉ የማድሪዱን የአጥቂ ተጫዋቾች መቋቋም ሳይችል መቅረቱ ይታወሳል።

ቼሊኒ ጫማውን ባይሰቅልም እድሜው ከመሄዱ አንፃር በቀጣይ ከጡረታው በፊት ይህን ዋንጫ ለማንሳት እድለኛ ካልሆነ በቀር የመሳካት እድሉ ወደ ማክተሙ ተጠግቷል።

5) አማካይ/ተከላካይ – ሉተር ማቲያስ

ጀርመናዊው ከሳጥን እስከ ሳጥን በመጫወት ይታወቅ የነበረው ሉተር ማቲያስ የቻምፕየንስ ሊግን ዋንጫ ለማንሳት 3 ደቂቃዎች ብቻ ቀርተውት ነበር።

ለባየርሙኒክ እየተጫወተ 1999 ላይ በካምፕ ኑ በፍፃሜ ጨዋታ ከማንችስተር ዩናይትድ ጋር ቢደርሱም ድራማዊ በሆነ መልኩ በመጨረሻ ደቂቃ ላይ ያስተናገዱት ሁለት ጎሎች ዋንጫውን ተነጥቀዋል።

ሉተር ማቲያስ በቻምፕየንስ ሊጉ የመጨረሻ ተሳትፎው

ሉተር ማትያስም ጫማውን ከመስቀሉ በፊት በመስመር ተከላካይነት በመጫወት የረጅም ጊዜ የጨዋታ ጊዜውን አጠናቋል።

በዛ ጨዋታ ላይ የጋናዊው ኩፎር ንዴት በጨዋታው መጨረሻ ላይ የሚታወስ ሲሆን በእንግሊዙ ክለብም እስከ አሁን ድረስ በታላቅ ስኬቱ አመቱ ይታወሳል።

6) አማካይ – ፓትሪክ ቪየራ

ቁመተ ለግላጋው አማካይ ከመድፈኞቹ ጋር በፕሪምየርሊጉ ያሳለፈው ቆይታ በውጤታማነቱ ይጠቀሳል።በተለይ ሳይሸነፍ በተጓዘው የአርሰናል ስብስብ ውስጥ ጉልህ ሚና ነበረው።

ቪየራ በጁቬ

ቪየራ 2006 ላይ መድፈኞቹ በታሪካቸው ሊያሳኩት ከተቃረቡበት የቻምፕየንስ ሊግ ዋንጫ በባርሴሎና ተሸንፈው ህልማቸው ካልተሳካበት አንድ አመት ቀደም ብሎ ሀይበሪን ተሰናብቷል።

ቪየራ ለጁቬንቱስ እና ለኢንተር ሚላን ጭምር መጫወት ቢችልም የአውሮፓ ታላቁን ዋንጫ ለማሸነፍ አልታደለም።

7) አማካይ – ማይክል ባላክ

ጀርመናዊው አማካይ በቻምፕየንስ ሊግ ከሚቆጩ ተጫዋቾች ውስጥ አንዱ ነው።93 ጊዜ በመጫወት የውድድሩ ሰፊ ልምድ ቢኖረውም ሁለት ጊዜ ለፍፃሜ ደርሶ ሁለቱንም ተሸንፏል።

ባላክ ለሁለተኛ ጊዜ ዋንጫ ካጣ በኋላ

2002 ላይ በአስደናቂው የባየርሊቨርኩሰን ስብስብ ውስጥ ተካቶ የእንግሊዞችን ሀያል ቡድኖች በመርታት ለፍፃሜ ቢደርስም የማትረሳዋ የዚዳን ጎል ታክሎ ሪያል ማድሪድ 2-1 ማሸነፍ ችሎ እንደነበር ይታወሳል።

ባላክ በድጋሚ በቼልሲ ማሊያ ዋንጫ ለማንሳት እጅግ ተቃርቦ የነበረበት የ 2008 ቱ የቻምፕየንስ ሊጉ ውድድር በመለያ ምት ማንችስተር ዩናይትድ ከጉሮሯቸው ፈልቅቆ ቀምቷቸዋል።

8) አማካይ – ፓቬል ኔድቬድ

ቼካዊው አማካይ በላዚዮ እና በጁቬንቱስ ድንቅ አመታትን አሳልፏል።ወደ ጎን በተኛው ፀጉሩ የሚለየው ኔድቬድ 2003 ከአሮጊቷ ጋር ለፍፃሜ በቅጣት ካመለጠው ውጪ ባለ ትልቁን ጆሮ ዋንጫ ለማንሳት አልተቃረበም።

ኔድቬድ እና ዚዳን (2003)

ከላዚዮ ጋር አንድ ጊዜ በሩብ ፍፃሜ እንዲሁም ሁለት ጊዜ ከጁቬንቱስ ጋር ለግማሽ ፍፃሜ መድረስ ችሏል።

አማካይ እና የመስመር ተጫዋቹ ኔድቬድ ወደ ጎል የሚጠመዝዛቸው ኳሶቹ ተለይቶ የሚታወቅ ስመገናና ነገርግን የቻምፕየንስ ሊግ ዋንጫ ለማንሳት ያልታደለ ነው።

9) አጥቂ – ሄርናን ክሪስፖ

በፓርማ፣በላዚዮ፣በኢንተር፣በሚላን እና በቼልሲ የተጫወተው ክሪስፓ 2005 ላይ ሊያስታውሰው የማይፈልገው ጠባሳ በቻምፕየንስ ሊጉ አጋጥሞታል።

ለሚላን እየተጫወተ በቻምፕየንስ ሊጉ ስታንቡል ላይ ከሊቨርፑል ጋር ለፍፃሜ ተፋጠጡ።የመጀመሪያ ግማሽም 3-0 በመምራት ዋንጫውን ያሸነፉ መሰሉ።

2005 ስታንቡል ላይ ሁለት ጎል አስቆጥሮ ዋንጫ ያላነሳው ክሪስፖ

በሁለተኛው ግማሽ ግን ነገሮች መልካቸውን ቀይረው ሊቨርፑል አስደናቂ መንሰራራት በማድረግ ጨዋታውን ማሸነፍ እንደቻለ ይታወሳል።

የሚላን የቡድን አባል የነበረው ክሪስፖ በዛ ጨዋታ ላይ ሁለት ጎሎችን ቢያስቆጥርም በመጨረሻ ቡድናቸውን አሸናፊ አላደረገውም።

10) አጥቂ – ዝላታን ኢብራሂሞቪች

ዝላታን እና የቻምፕየንስ ሊግ ዋንጫ ሊዋደዱ አልቻሉም። በትላልቅ የአውሮፓ ቡድኖች ጋር 120 ጊዜ መሳተፍ ቢችል ዋንጫ ማንሳት አልቻለም።

ይልቁኑ በሚያስቆጭ መልኩ ጥሏቸው የሄዳቸው ክለቦች እሱ ቡድኑን በለቀቀ በቀጣይ አመት ላይ የዋንጫ ባለቤት መሆን ችለዋል።

እድለ ቢሱ ዝላታን

ከኢንተር ወደ ባርሴሎና ሲያቀና በቀጣዩ አመት ኢንተር ሚላን ከጆሴ ሞሪንሆ ጋር በመሆን የቻምፕየንስ ሊግ ዋንጫን አነሳ።

ከባርሴሎና ደግሞ ወደ ሚላን ካቀና በኋላ በቀጣዩ አመት የካታላኑ ቡድን የቻምፕየንስ ሊግ ዋንጫን ማሸነፉ ይታወሳል።

ዝላታን እና ቻምፕየንስ ሊግ ፊት እና ጀርባ ናቸው ቢባል የማይስማማ ይኖር ይሆን?

11) አጥቂ – ሮናልዶ ልዊስ ናዛሪዮ ዴሊማ

የአጥቂዎች ቁንጮ መሆኑን ብዙዎች የሚመሰክሩለት ብራዚላዊው ሮናልዶ ሁለት ጊዜ የአለም ዋንጫን በማንሳት ቢሞሸርም የቻምፕየንስ ሊጉን ግን ሳያሸንፍ ጫማውን ሰቅሏል።

የሮናልዶ ሀዘን እና የትርዚጌት ደስታ (2003)

በማድሪድ፣በኢንተር እንዲሁም ከባርሴሎና ጋር የነበረው ቆይታ ለድል ሊያበቃው አልቻለም።

2003 ላይ ማንችስተር ዩናይትድ ላይ ሀትሪክ በመስራት ዋንጫውን ለማንሳት የተቃረበ ቢመስልም በግማሽ ፍፃሜው በጁቬንቱስ ተሸንፈው ከመንገድ ቀርተዋል።

አሰልጣኝ – አርሴን ዌንገር

ለረጅም አመታትን መድፈኞቹን በታላቁ መድረክ መምራት ቢችሉም ለዋንጫ ተቃርበው የነበሩት 2006 ላይ ነበር።

በወቅቱ ባርሴሎናን ለመርታት 14 ደቂቃ ቢቀራቸውም ኤቶ እና ቤሌቲ ባስቆጠሩት ጎሎች ተሸንፈው ዋንጫውን ሳያነሱ ቀሩ።

ቬንገር 2006 ላይ

ቬንገር አሁን አሁን ደግሞ ከሞቁበት የቻምፕየንስ ሊጉ ተሳትፎ እየራቁ የሚገኙ ሲሆን በቀጣይ አመት ላይም ለመሳተፍ በዩሮፓ ሊግ አቋራጭ መንገድ በመጠቀም ከፊታቸው የአራት 90 ደቂቃዎች ላይ ውጤታማ መሆን ይጠበቅባቸዋል።

የቻምፕየንስ ሊጉን ዋንጫ ማንሳት ያልቻሉ ተጫዋቾች አሰላለፍ(433)

Advertisements