የሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ድልድል መቼ ይወጣል? ማንን ከማን ጋር ሊያገናኝስ ይችላል?

በዚህ ሳምንት በተደረጉ የሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታዎች ድራማዊ ክስተቶች የታዩበት ሆኖ የግማሽ ፍፃሜውን መቀላቀሉ የቻሉ አራት ክለቦች ተለይተውበታል።

ተከታዩ ፅሁፍም የግማሽ ፍፃሜው እና ፍፃሜው መቼና የት እንደሚደረግ እንዲሁም ማን ከማን ጋር ሊገናኝ ይችላል? የሚሉትን ጥያቄዎች ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮችንም ይመለከታል።

የግማሽ ፍፃሜ ድልድሉ መቼ ይወጣል?

የሻምፒዮንስ ሊጉ የግማሽ ፍፃሜ የዕጣ ድልድል ዛሬ (አርብ) ከቀትር በኋላ 8፡00 ሰዓት በሲዊዘርላንዷ ከተማ ኒዮን የሚከናወን ይሆናል።

የዕጣ ድልድሉም ወድግማሽ ፍፃሜው ማለፋቸውን ያረጋገጡት ሊቨርፑል፣ ሮማ፣ ሪያል ማድሪድና ባየር ሙኒክን የሚያገናኝ ይሆናል።

የግማሽ ፍፃሜ የዕጣ ድልድል በስዊዘርላንድ፣ ኒዮን የሚወጣ ይሆናል

በዕጣ ድልድሉ እርስ በእርስ ሊገናኙ የማይችሉ ክለቦች ይኖራሉ?

የሉም። በውድድሩ በዚህ የማጣሪያ ደረጃ የትኛውም ክለብ ከየትኛውም ክለብ ጋር ሊገናኝ ይችላል።

የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎቹ መቼ ይደረጋሉ?

የግማሽ ፍፃሜው የመጀመሪያ ጨዋታዎች ማክሰኞና ሚያዝያ 17 እና ረቡዕ ሚያዝያ 18 ሲደረጉ፣ የመልስ ጨዋታዎቹ ደግሞ በተከታዩ ሳምንት ማክሰኞ ሚያዝያ 23 እና ረቡዕ ሚያዝያ 24 የሚካሄዱ ሆነው በዕጣ ድልድሉ የመጀመሪያው ዕጣ የወጣላቸው ክለቦች የመጀመሪያውን ጨዋታቸውን በሜዳቸው የሚያደርጉ ይሆናል።

የፍፃሜ ጨዋታው የሚደረግበት የኪየቭ ኦሎምፒክ ስታዲየም

የፍፃሜው ጨዋታ መቼ ይደረጋል?

የ2018 የሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ ቅዳሜ ግንቦት 18 ምሽት 3፡45 ላይ በዩክሬኗ ከተማ ኪየቭ ኦሎምፒክ ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል።

Advertisements