በህይወቷ ለሁለተኛ ጊዜ በሮጠችበት የማራቶን ውድድር ሁለተኛ የወጣችው ነርስ አነጋጋሪ ሆናለች


በአለማችን በዕድሜ ትልቁ የሆነው የቦስተን ማራቶን ለ122ኛ ጊዜ ትናንት ሲካሄድ 185 ዶላር ከፍላ ለውድድሩ የተመዘገበችው አሜሪካዊት ነርስ ሁለተኛ ሆና ውድድሩን በመጨረስ 75000 ዶላር አሸናፊ ሆናለች፡፡

የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ ተሳታፊዋ ዲዝሪ ሊንደን ከ1985 በኋላ ውድድሩን ያሸነፈች የመጀመሪያ አሜሪካዊት የሆነችበትን ውጤት ብታስመዘግብም የአለምን አትሌቲክስ ቀልብ የሳበው በሁለተኝነት ውድድሩን ያጠናቀቀችው የ26 አመቷ ሳራ ሴለርስ ናት፡፡

ሳራ የሰኞው የቦስተን ውድድር ሁለተኛ የማራቶን ሩጫዋ ሲሆን ከዚህ በፊት ወደዚህ ውድድር እንድትሸጋገር ያደረጋትን ማራቶን በሁታህ አድርጋ አሸንፋለች፡፡

በትምህርት ቤት ህይወቷ በሩጫ ውድድሮች ላይ ትሳተፍ እንደነበረች የተነገረላት የጤና ባለሙያ በጉዳት ምክንያት ከውድድሮች ተገላ እንደነበር ዘገባዎች አትተዋል፡፡

ስፖንሰር ወይም ወኪል አልባዋ ሳራ ሴለርስ በስራዋ የጤና ባለሙያ (ነርስ) እንደመሆኗ ልምምዷን ከሌሊቱ 10 ሰዓት በመነሳት ስታደርግ የቆየች ሲሆን ከልምምዷ በኋላም ንጋት 12:30 ወደመደበኛ ስራዋ በመሄድ ስትሰራ ቆይታለች፡፡

ውድድሩ በከፍተኛ ዝናብና ነፋስ የታጀበ የነበረ ሲሆን ይህም ለረጅም ርቀት በውድድረ መሪነት ተቀምጣ የነበረችውን ኢትዮጵያዊ አትሌት ማሚቱ ዳስቃ ሩጫውን አቋርጣ እንድትወጣ አስገድዷታል፡፡

ስኬቷን ተከትሎ ከተለያዩ አቅጣጫዎች አድናቆት የጎረፈላት ሴለርስ 42.195 ኪሎ ሜትሩን ከአሸናፊዋ አትሌት በአንድ ደቂቃ ብቻ ዘግይታ ከጨረሰች በኋላ ከሚድያ አካላት ጋር በነበራት ቆይታ “ሙሉ ውድድሩን በዝናብና በነፋስ መሮጤ የልብስ ማጠቢያ ማሽን ውስጥ የገባው ያህል እንዲሰማኝ አደርጓል ፤ አንዳንድ ሰዎች እንደምሮጥ ያውቃሉ፡፡በዚህ ደረጃ መሮጤ ግን ሁሉንም ማስገረሙ አልቀረም” ብላለች፡፡

ከትናንቱ ውድድር በኋላ ዛሬ ወደመደበኛ የህክምና ስራዋ እንደምትመለስ የተናገረችው አስገራሚዋ ተወዳዳሪ ከዚህ በኋላ መሉ በሙሉ ወደሩጫው ጠቅልሎ ስለመግባት በቀረበላት ጥያቄ በሳቅ የታጀበ ምላሽ የሰጠች ሲሆን “ስራዬን እሰራለሁ ፤ መሮጤን ግን በፍፁም አላቆምም” የሚል አጭር ምላሿን አስቀምጣለች፡፡

በዚሁ የቦስተን ማራቶን የወንዶቹን ውድድር ያሸነፈው ጃፓናዊ ዩኪ ካዋኡቺ በተመሳሳይ ተጠባቂ የነበሩ አትሌቶችን ድል ማድረግ የቻለ ሲሆን መንግስታዊ በሆነ ድርጅት ውስጥ በሳምንት ለ 40 ሰዓታት የሚሰራና ከሳምንቱ ቀናት በአንዱ ብቻ የሩጫ ልምምዱን የሚያደርግ ግለሰብ መሆኑ የዘንድሮውን የቦስተን ማራቶን አስገራሚ ገፅታን አላብሶት አልፏል፡፡

Advertisements